በጁንታው ላይ የተወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ የእናቶችን እምባ ያበሰ ነው-- የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
በጁንታው ላይ የተወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ የእናቶችን እምባ ያበሰ ነው-- የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ
ባህር ዳር ህዳር 07 /2013 (ኢዜአ) በህወሃት የጥፋት ቡድን ላይ የተወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ በየጊዜው ልጆቻቸውን በሞት የሚነጠቁ እናቶችን እምባ ያበሰ መሆኑን የአማራ ክልል ምክር ቤት -አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅ ሰሙ ማሞ ገለጹ።
የአማራ ክልል ሴቶች ፎረም ተመራጭ አመራሮች በእንጅባራ ከተማ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
አፈ-ጉባኤዋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የህወሓት አሸባሪ ቡድን በአማራ ህዝብ ላይ በነበረው የከረረ ጥላቻ አቅዶ የዘር ማጥፋት ስራ አከናውኗል።
"ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲ ልከው ለማስተማር ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ እናቶች በምትኩ የልጆቻቸውን አስከሬን እንዲቀበሉ ሲደረጉ ቆይተዋል" ብለዋል።
የህወሓት የጥፋት ቡድን ህዝቡ በገዛ ሀገሩ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ሃብት አፍርቶ የመኖር መብቱ ነፍጎ ለስቃይ መዳረጉን አውስተዋል።
ቡድኑ በህዝቡ ላይ የነበረውን የመረረ ጥላቻ የማይካድራ ከተማ ነዋሪዎችን በግፍ በመጨፍጨፍ በግልፅ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
ጁንታው በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸሙ በተወሰደ ህግን የማስከበር እርምጃ ከምንም በላይ ለእናቶች ትልቅ እፎይታ የሰጠ ነው ብለዋል።
የህወሓት የጥፋት ቡድን መውደቅ ደስታው ለማንኛውም የኢትዮጵያ እናቶች ቢሆንም በተለይ ለአማራ ክልል እናቶችን እምባ ያበሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ሴቶችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች የእኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መብት እንዲጠበቅም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ሴቶች፣ ህጻናት፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሉባባ ኢብራሂም ናቸው።
ከቤት ንብረታቸውና ከመሬታቸው የሚፈናቀሉ ሴቶች በርካቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤እያንዳንዱ የሴቶች ፎረም አመራር ሴቶችን በማንቃትና በማስተማር ሴቶች መብታቸውን ማስከበር የሚችሉበትን አግባብ እንዲረዱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተለይም የመሬት አስተዳደር ተቋማት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፍታዊ ያልሆነ የሃብት አጠቃቀም በማስተካከል በኩል መስራት እንደሚጠቀምባቸው አሳስበዋል።
ምክር ቤቱም ከየአቅጣጫው የሚደርሱትን ጥቆማዎች በመቀበል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ እየሰራ ነው እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የክልሉ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ትልቅ ሰው ይታያል በበኩላቸው በክልሉ ያሉ የተለያዩ የሴቶች አደረጃጀቶች በቅንጅት በመስራት በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርሰውን እንግልትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት መጀመሪያ የተለያዩ የሴቶች አደረጃጀቶች መግባባትና መቀናጀት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
በክልሉ ሴቶችን ያቀፉ ደራሲያን፣ አካል ጉዳተኛ ማህበራትና ሌሎችም ተቀናጅተው በመስራትና መብትን በማስከበር ረገድ ክፍተቶች እንደሚስተዋልባቸው ጠቁመዋል።
ለቀጣይ የቅንጅት ሥራው ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፤ በተያዘው ወርም ቅንጅታዊ አሰራሩን ለማጎልበት የንቅናቄ መድረኮች እንደሚዘጋጁ አስታውቀዋል።
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከታህሳስ 5 ቀን 2013ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤን ጨምሮ ከዞን እስከ ወረዳ ያሉ የሴቶች ፎረም ተመራጭ አመራሮች ተሳተፈዋል።