ቀጥታ፡

የአስቸኳይ ሕክምና መመሪያን ለመተግበር ሶስት ተቋማት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2013(ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስና የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የአስቸኳይ ሕክምና መመሪያን ለመተግበር ስምምነት ተፈራረሙ። 

ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሰሃረላ አብዱላሂ፣ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታ እና የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ፈርመዋል።  

በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ የትራንፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ተገኝተዋል።

የተሽከርካሪ አደጋ ደርሶባቸው የአስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ለማከም የአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት መመሪያ ቁጥር 1/2006 ቢወጣም ውጤት እየተመዘገበበት አይደለም።  

ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በአገሪቷ ከሚገኙ የሕክምና ተቋማት መካከል አስቸኳይ ሕክምናውን የሚሰጡት ቁጥር ዝቅተኛ ነው።  

የሶስቱ ተቋማት ስምምነትም ችግሩን ለመፍታት በተለይም ቅንጅትን በማጠናከር የአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት መመሪያው እንዲተገበር ለማስቻል መሆኑ ተገልጿል።    

መመሪያው አደጋ የደረሰባቸው ዜጎች እስከ ሁለት ሺህ ብር የሚደርስ ነጻ ሕክምና እንደሚያገኙ የሚያስቀምጥ ቢሆንም ኀብረተሰቡ ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ የለውም ነው የተባለው።

የኤጀንሲው የኦፕሬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አዲል አብዱላሂ የስምምነቱን ይዘትና ዓላማ ባቀረቡበት ጽሁፍ ይህንኑ አብራርተዋል።   

በስምምነቱ መሰረት ኤጀንሲው ኅብረተሰቡ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ስለ አስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን የሚሰራ ይሆናል።   

በመመሪያው አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ መሙላትና ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ማሻሻልም የኤጀንሲው ድርሻ ነው ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር፣ በጤና ቢሮዎችና በሕክምና ተቋማት የመመሪያው አተገባበር ላይ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ እልባት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ መስራትም እንዲሁ።  

አቶ አዲል እንዳብራሩት በጤና ሚኒስቴር በኩል ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመሪያው መሰረት ተግባራዊ ማድረጋቸውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል።  

ከተመደበላቸው ተዘዋዋሪ ፈንድ 75 በመቶውን የተጠቀሙ ተቋማት ኦዲት ተደርገው ተጨማሪ ፈንድ እንዲለቀቅላቸውም ያደርጋል።  

ጤና ሚኒስቴር ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ቋሚ አምቡላንስ እንዲመደብ እንደሚያደርግ የተናገሩት ዳይሬክተሩ መንገዶች ዳር ለሚኖሩ ነዋሪዎች፣ ለደንብ አስከባሪዎች፣ ለትራፊክ ፖሊሶችና ለበጎ ፍቃደኞች የተሽከርካሪ አደጋ የአስቸኳይ ሕክምና ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።

የፌዴራል ፖሊስ በኤጀንሲው የተዘጋጀውን ቅጽ መሰረት በማድረግ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎችን የጉዳት ዓይነት ሞልቶ ለሚመለከተው አካል ያቀርባል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ተጎጂዎችን ወደ ሕክምና ተቋማት መላክና ለተቋማቱም አስፈላጊውን መረጃ መላክ ከፌዴራል ፖሊስ ከሚጠበቁ ተግባራት መካከል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ አስቸኳይ ሕክምና በማጣታቸው ምክንያት በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ ጉዳቶች ወደ ከፋ ደረጃ ሲደርሱ ይታያል ብለዋል።  

አሁንም በዜጎች ላይ ቀላል የማይባል ሞትና አካል ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ መመሪያውን በተቀናጀ መንገድ መተግበር ችግሩን ለማቃለል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።  

አዋጁ በሚያዘው መሰረት ለሞትና  ለአካል ጉዳት  የሚከፈለው አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ በቂ አለመሆኑን መለየታቸውን ገልጸው፤ የካሳ ክፍያውን ለማሻሻል በጥናት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።  

ወይዘሮ ወርቅነሽ እንዳሉት ኤጀንሲው ከጤና ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከክልሎች ጋር መልካም የሚባል ቅንጅት እየፈጠረ ነው።   

የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞጎስ በበኩላቸው ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች ከተሽከርካሪ አደጋ በኋላ ወደ ጤና ተቋም ሳይደርሱ ለህልፈት ይዳረጋሉ ብለዋል።  

የጤና ተቋማት አስቸኳይ ሕክምና ላይ የሚሰጡት ግልጋሎት መሻሻል ቢያሳይም የበለጠ መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአገሪቷን ብልጽግና ለማረጋገጥ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።    

የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለቀነስ የመንገዶችን ዲዛይን ከማሻሻል ጀምሮ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅሰው ለዚህም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

"መመሪያውን ለመተግበር መፈራረም ብቻውን በራሱ ግብ አይደለም" ያሉት ሚኒስትሯ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።  

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው የመንገድ ትራፊክ አደጋ በገዳይነቱ በ9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም