ቀጥታ፡

በልማት እቅዱ ለማምጣት የታሰበው የኢኮኖሚ እድገት በዜጎች ጓዳ እንዲደርስ ግብ ተይዟል...የፕላንና ልማት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2013(ኢዜአ) በ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ለማምጣት የታሰበውን የኢኮኖሚ አድገት በዜጎች ጓዳ እንዲደርስ የማድረግ መሰረታዊ ግብ መያዙን የፕላንና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢኮኖሚ እድገቱን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ብዝሃ የሆነ የእድገት ምንጭ እንዲኖራት በትኩረት እንደሚሰራም ተገልጿል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ረቂቅ ሰነድ ይዘትን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ይፋ ለማድረግና ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንዲረዳ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

ረቂቅ ሰነዱ ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም ተግባራዊ በሚሆነው የልማት እቅድ ኢትዮጵያ በአማካይ በየዓመቱ የሚኖራት ጠቅላላ የአገር ውስጥ የምርት መጠን እድገት 10 በመቶ እንደሚሆን ግምቱን ያስቀምጣል።

በ10 ዓመት ውስጥ የነፍስ ወከፍ ገቢን በአማካይ በስምንት በመቶ እድገት ለማስመዝገብና በ2022 ዓ.ም የአንድ ኢትዮጵያዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 2 ሺህ 201 የአሜሪካ ዶላር የማድረስ እቅድ ተይዟል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ በ10 ዓመት ለማሳካት የታሰበው የኢኮኖሚ እድገት ጥራት ያለው እንዲሆን ምን ታስቧል? እድገቱ በዜጎች ሕይወት ላይ የሚታይ ለውጥ እንዲያመጣ የሚሰሩ ሥራዎች ምንድን ናቸው? እና በልማት እቅዱ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ያሉ መደላድሎች ምን ይመስላሉ? የሚሉ ሀሳቦችን በዋናነት አንስተዋል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ከዚህ በፊት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱና በሌሎች የልማት እቅዶች የኢኮኖሚ እድገት ፈጣን ነው ቢባልም በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ለውጥ እንዳላሳየ ገልጸዋል።

በዚህም ዜጎች የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል ቢባልም በሕይወታቸው የተቀየረ ነገር ስለሌለ እድገቱ ዜጋ ተኮር ስለመሆኑና የእድገት ሪፖርቱም ላይ ጥያቄዎች ያነሱበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል።

በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና ተግባራት የዜጎች ሕይወት በምን አይነት መልኩ ተለውጧል? የሚለው ጉዳይ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ ማሳያ መሆኑንም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እስከዛሬ ሲታይ የነበረው መንግስት በመሰረተ ልማትና በተለያዩ መስኮች የሚያፈሰው መዋዕለ ነዋይን ታሳቢ ያደረገና ሕብረተሰቡን ያላማከለ እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህ ረገድ የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅዱ በባለፉት ጊዜያት ከነበረው የእድገት መለኪያ ተሞክሮ በመውሰድ የሚመዘገበው የኢኮኖሚ እድገቱ በሰዎች ላይ መታየት የሚችል ለውጥ እንዲያመጣ የማድረግ ግብ እንዳለው ተናግረዋል።

ለዚህም የተለያዩ አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚሆኑ ነው ኮሚሽነሯ ያስረዱት።

በልማት እቅዱ ቱሪዝምን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎችን በማካተት ብዝሃ የሆነ እድገት ለማስመዝገብ እቅድ መያዙንም ነው ዶክተር ፍጹም የገለጹት።

በመሪ የልማት እቅዱ ኢትዮጵያ በሚኖራት መዋቅራዊ ሽግግር፣ ፖሊሲና የአሰራር ስርዓቶች ላይ ማሻሻያዎች ማድረግን ጨምሮ ምቹ መደላድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።

ግብርናውን በማዘመን በዘርፉ የሚገኘውን እድገት መጨመር፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ድርሻ ማሳደግ እንዲሁም ግብርናና ኢንዱስትሪን በማሳደግ የአገልግሎት መስኩን ድርሻ ለማጎልበት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ፍጹም ገለጻ የግሉን ዘርፍ በኢኮኖሚ ማሳደግ እንዳለ ሆኖ መንግስት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት፣ ፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች በማዘጋጀትና ለእድገቱ የሚሆን አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር በኢኮኖሚው ላይ ተሳትፎ ያደርጋል።

በእቅዱ የኢኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እምርታ በማምጣት ሁለተናዊ እድገት ለማምጣት እንደሚሰራም ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።

"በአጠቃላይ በመሪ ልማት እቅዱ በተቻለ መጠን ዜጎችንና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አሳታፊ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል" ብለዋል።

ለዚህም ከ100 በላይ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ከ21 በላይ የውይይት መድረኮች መዘጋጀታቸውን ዶክተር ፍጹም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት በተለየ መልኩ ተቋማት የተሰጣቸውን እቅድ መፈጸም ሳይሆን በየዘርፉ የራሳቸውን የልማት እቅድ በተናበበ መልኩ ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

መሪ የልማት አቅዱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱንና በምክር ቤቱ ሕግ ሆኖ እንደሚጸድቅና ሕጉ ፈጻሚ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑም የእቅዱን አፈጻጸም የሚከታተልና የሚቆጣጠር የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።

መገናኛ ብዙሃንም በልማት እቅዱ ተፈጻሚነት ላይ ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ኮሚሽነሯ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም