የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተቀበሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተቀበሉ
ባህር ዳር ሀምሌ 13/2010የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገዱ አንዳርጋቸው ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተበረከተላቸውን የ “አመራርና ማህበራዊ ለውጥ'' የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተቀበሉ። የሃሮሚያ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና የተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጀይላን ወልይ የክብር ዶክትሬቱ በተሰጠበት ስነ ስርዓት እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው የሰጠው የዶክትሬት ዲግሪ የርዕሰ መስተዳደሩን የለውጥ አመራር ብቃት በመመዘን ነው። የክብር ዶክትሬት ዲግሪው በባህር ዳር ከተማ መጥቶ እንዲሰጣቸው የተደረገውም በዩኒቨርሲቲው የምረቃ ስነስርዓት ላይ በስራ መደራረብ ባለመገኘታቸው እንደሆነ ገልፀዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ በኢትዮጵያ አንድነት እንዲመጣና የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመዘገብ ላደረጉት ትግል የተበረከተ መሆኑን ተናግረዋል። “የክቡር ዶክተር ገዱ አንዳርጋቸው በጥልቅ ፖለቲካዊ እውቀት፣ እውነተኛ ሃገር ወዳድነት፣ ብልሃት የተሞላበት አመራር በመስጠት ተራማጅ አመራር የሰጡ ናቸው'' ብለዋል። “ህዝባዊ መሰረት ያለው ፖለቲካዊ ትግል መጨረሻው አሸናፊነት መሆኑን አጥብቀው ይዘው የሚንቀሳቀሱና ኢትዮጵያ በህዝቦች አንድነትና መፈቃቀር ላይ ብቻ ተመስርታ መቀጠል የምትችል ሃገር ስለመሆኗ ያስተማሩ በሳል አመራር ናቸው'' ብለዋል። “ዩኒቨርስቲው ላስመዘገቡት የአመራር ብቃት የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን ሲሰጣቸው በቀጣይ የጀመሩትን የህዝባዊ አመራርነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጭምር ነው'' ብለዋል። ''ዩኒቨርሲቲው የሰጠኝ እውቅና ቀደም ሲል ላበረከትኩት አነስተኛ አስተዋጽኦ ቢሆንም ለቀጣይ በኃላፊነት መንፈስ የበለጠ ተግቼ እንድሰራ የሚያተጋኝ ነው'' ያሉት ደግሞ ርእሰ መስተዳድሩ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው። “በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝቦች እየጠየቁ ያሉት ፍትህ፣ ነፃነትና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን አጠንክሮ የሚያስቀጥል አመራር እንዲኖር ነው'' ብለዋል። ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሃገር እንደመሆኗ መጠን ይህን ብዝሃነት ግምት ውስጥ አስገብቶ የሚመራ የለውጥ መሪ እንደሚያስፈልጋት ጠቁመው ይህንን ህዝባዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝም በተሻለ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች እርስ በእርሳቸው የሚፈቃቀዱ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የሚያዳብሩ፣ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ብዝሃነትን ለሚያስተናግዱ ሃገራት ምሳሌ መሆን የምትችል ሃገር እንድትሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ “መሪ የናፈቀው የአማራ ክልል ህዝብም ትንንሽ የለውጥ ሙከራዎችን እያጎለበተና እያደነቀ ደጀን ሆኖ ወደፊት እንድንራመድ እያደረገ ነው'' ብለዋል፡፡ በመሆኑም በዩኒቨርስቲው የተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት ለበለጠ ለውጥ እንዲሰሩ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመው፤ ለዩኒቨርሲቲው ክብርም አመስግነዋል፡፡ በባህር ዳር አቫንቴ ብሉናይል ሆቴል በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ የክልል አመራሮችን ጨምሮ ወጣቶች የሃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።