ቀጥታ፡

ሴቶች የሚደርስባቸውን የሠብዓዊ መብት ረገጣ ለማስቀረት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2013 (ኢዜአ) በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የሠብዓዊ መብት ረገጣ ለማስቀረት ሴቶች ለራሳቸው ትኩረት ሰጥተውና ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

የሴቶች የሠብዓዊ መብት ቀን "የሴቶች ሠብዓዊ መብት ይጠበቅ፤ ሠላም ለሴቶች ከጓዳ እስከ ሃገር" በሚል መሪ ሃሳብ በባለድርሻ አካላት ተከብሯል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቀረትና የሠብዓዊ መብት እሴቶች ቁርጠኝነትን አፅንኦት ለመስጠት "የሴቶች መብት የሠብዓዊ መብትም ነው" በሚል ርዕስ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የቅንጅቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን እንደሚሉት 'ሴቶች ሠብዓዊ መብታቸው የሚከበረው ደካሞች ወይም ምስኪኖች ስለሆኑ ሳይሆን ሰው ስለሆኑ ነው'፡፡

በመሆኑም ኅብረት ፈጥረው ለሴቶች የሠብዓዊ መብት ጥያቄዎች ምላሽ ማስገኘትና ታች ሆነው ለመብታቸው የሚታገሉ ሴቶችን በመደገፍ ወደላይ ነጥረው እንዲወጡ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሠብዓዊ መብት ምክር ቤት ከፍተኛ ባለሙያዋ ወይዘሮ መስከረም ገስጥ  በበኩላቸው የሴቶች ሠብዓዊ መብት ባልሰረፀበት ማኅበረሰብ ለሚያጋጥሙ ችግሮች 'እኛ ሴቶች ራሳችን የመፍትሄ አካል ልንሆን ይገባል' ነው ያሉት፡፡

በሴቷ ላይ የሚደርሱ ፆታዊም ሆነ ስነልቦናዊ ጥቃቶችን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ችግሩ እንዲባባስ ስለሚያደርግ ወደ ሕግ አካል እንድትሄድ በማድረግ 'ድርሻን መወጣት ያስፈልጋል' ሲሉም አክለዋል።

ደራሲና ገጣሚ የምወድሽ በቀለ ደግሞ የኅብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየር መገናኛ ብዙሃን ትልቅ መሳሪያ መሆናቸውን አንስታለች፡፡

ብዙ ሴቶች ሃሳባቸውን በሚዲያ እንዲያንፀባርቁ ሲጠየቁ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ያነሳችው የምወድሽ 'ይህ ስህተት ነው እናቶች ለሴት ልጆቻችን መስራት እንደምንችል በተግባር እያሳየን ማሳደግ አለብን' ብላለች፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ሴቶች በፖለቲካው መስክ 51 በመቶ በከፍተኛ የመንግስት የስልጣን እርከን ላይ ቢመጡም ሴት ሚኒስትሮቻችን ወደ ታች ወርደው የሴቶችን ችግሮች ለመፍታት ሲሰሩ አይታዩም ብላለች፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ሁሉ "የሴቶች ጥቃት ይመለከተኛል" በማለት ለሚሰሩ የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ሌሎች አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በምክክር መድረኩ በሠብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩና በዘርፉም ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም