ቀጥታ፡

የማንነት ጥያቄ በማቅረባችን ወያኔ በግፍ አስሮን ቢቆይም ሰራዊቱ ነፃ ስላወጣን ተደስተናል-- ታስረው የነበሩ ዜጎች

አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2013 (ኢዜአ) የማንነት ጥያቄ በማቅረባችን የህወሃት ቡድን በግፍ አስሮን ቢቆይም ሰራዊቱ ነፃ ስላወጣን ተደስተናል ሲሉ ከእስራት የተፈቱ የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከእስረኞች መካከል አቶ ብርሃኑ በላይ፣ አቶ ዳርጌ ከበደና ወይዘሮ ትህንዋ አገዞም በህወሃት ቡድን በግፍ ታስረው ስለደረሰባቸው ችግር ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በህገ ወጡ የህወሓት ቡድን እጅ ውስጥ ከገባሁ ጀምሮ በአምባ አላጌ፣ በእንዳመኾኒ፣ በማይጨውና በመቀሌ ማረሚያ ቤቶች ሲንከራተቱ እንደነበርም ገልጸዋል።

በመቀሌ ማረሚያ ቤት በነበሩበት ወቅት የመከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ እየተጠጋ ሲመጣ ሌሎች እስረኞች ሲፈቱ የራያ፣ የወልቃይትና የኤርትራ ሰላይ ብሎ ያሰራቸው ሰዎች ወደ ተምቤን ማረሚያ ቤት መወሰዳቸውንም ተናግረዋል።

የማንነት ጥያቄ ያነሳን 64 ሰዎች የሞት ፍርድ ቢፈረድብንም የዓቢ አዲ ማረሚያ ቤት ምክትል አስተዳዳሪ ኮማንደር ሐጎስ ውሳኔው እንዳይፀና በማድረጉ ተርፈናል ብለዋል።

አሁንም መንግሥት በህወሓት ላይ በወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ ከእስራት በመፈታታችን ተደስተናል ብለዋል አቶ ብርሃኑ።

“በእስር ቤት በቆየሁባቸው ጊዜያት የፀሐይ ብርሃን አላገኝም ነበር። ከፍተኛ ድብደባም ተፈፅሞብኝ ነበር" ሲሉም ተናግረዋል።

በእስር ቤት ቆይታቸው በአማርኛ እንዳይናገሩና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስርጭትን እንዳይከታተሉ ይደረጉ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ አቶ ዳርጌ ከበደ ናቸው።

በሕይወት ተርፈው ከቤተሰቦቻቸው በመገናኘታቸው ዳግም የመወለድ ያህል አድርገው እንደሚቆጥሩትም ተናግረዋል።

"የሞት ፍርድ ተፈርዶብን በመከላከያ ሰራዊት ጥረት ነፃ መውጣታችን በጣም አስደስቶኛል" ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ በራያ ማንነት ጥያቄ ምክንያት ታስረው የቆዩት ወይዘሮ ትህንዋ አገዞም ናቸው።

"በፅንፈኛው እጅ ወድቄ በህይወት ወደ ቤት እመለሳለሁ የሚል ተስፋ አልነበረኝም፤ አሁን ግን በሰላም ተመልሼ ከቤተሰቦቼ ጋር መገናኘት ችያለሁ" ብለዋል።

እስረኞቹ ከሞት ፍርድ አውጥቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ላደረጋቸው የአገር መከላከያ ሰራዊትና ወደ አላማጣ ሲገቡም ደማቅ አቀባበል ላደረገላቸው የከተማው ነዋሪ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የህወሃት ቡድን የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸውና በፖለቲካ ልዩነታቸው ምክንያት ያሰራቸው 64 የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች በህግ ማስከበሩ ነፃ መውጣታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም