ኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎቿን የመደገፍና መልሶ የማቋቋም ዝግጅቱ አላት- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎቿን የመደገፍና መልሶ የማቋቋም ዝግጅቱ አላት- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2013 ኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ዜጎቿን የመደገፍና መልሶ የማቋቋም ዝግጅቱና ብቃቱ ያላት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመቀሌ ከተማ በመገኘት ውይይት ማድረጋቸውም በክልሉ ሰለማዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚያረጋግጥ መሆኑ ተገልጿል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ በተግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰተዋል።
በማብራሪያቸው በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በህወሓት ቡድን ተፈጥሮ በነበረው ችግር ተፈናቅለው በሱዳን የሚገኙ ሠላማዊ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በሱዳን ተሰደው ከሚገኙት 40 ሺህ ያህል ዜጎች መካከል ከጁንታው ጋር የወንጀል ተሳተፎ ያላቸው ካሉ የመለየት ስራ እየተሰራ ሲሆን ሰላማዊ ዜጎች ግን ይመለሳሉ ብለዋል።
ቀደም ሲል የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን ጨምሮ ተፈናቅለው በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህን ለማድረግ የሚያስችል በቂ ልምድ ያላት በመሆኑ በራሷ አቅም ለመከወን የሚያስችል ዝግጅት እንዳላት አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል።
አሁን ላይ በክልሉ እየተሰሩ ባሉ የሰብዓዊ ድጋፎች 70 በመቶ የሚሆነውን ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግስት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሰብዓዊ ድጋፉ መድሃኒት፣ ምግብ የጫኑ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ የተለያዩ ከተሞች ተጓጉዘው በመድረስ ድጋፉ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመቀሌ ከተማ በመገኘት ከመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት ማድረጋቸውም በክልሉ ሰለማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በክልሉ አዲስ የተዋቀረው ጊዜዊ አስተዳደር መልሶ አካባቢውን ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ምክክር እያደረገ እንደሚገኝና የመብራት ስልክ እና የአየር ትራንፖርት መጀመር ሠላማዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአንዳንድ አለም አቀፍ ተቋማትና ግለሰቦች "ሰላም የለም" በሚል የመነዛው የሀሰት ወሬም ግርግር ከመፍጠር የሚያተርፉት ነገር ስላላ መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ አካላት ከጁንታው ጋር የጥቅም ግንኙነት ስላላቸው እኩይ አላማቸውን ለማስፈፀም ሲሉ የሀሰት ወሬያቸውን መቀጠላቸው አይቀርም ብለዋል።