ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሐይቆችን ከመጥፋት አደጋ ለመታደግ እየተሰራ ነው -- ባለስልጣኑ

ደሴ ታህሳስ 6/2013 (ኢዜአ) በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ሀይቆችን ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ ከወሎ ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሎጎ ሀይቅን ከመጥፋት አደጋ ለመታደግ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ በሀይቅ ከተማ እየመከረ ነው።

በባለስልጣኑ የኢኮ-ኅይድሮሎጅ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ዘሪሁን በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሐይቆች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

በሀይቆች ላይ ለተጋረጠው የመጥፋት አደጋ ምክንያቶች መካከል ልቅ ግጦሽ፣ የከተሞች መስፋፋት፣  የቆሻሻ አወጋገድ፣ የመጤ አረም መስፋፋት፣ ህገወጥ የእርሻ አጠቃቀምና አሳ ማስገር  ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የጣና፣ የሐዋሳና የሎጎ ሀይቆች ደግሞ ከፍተኛ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው እንደሆኑ አመልክተዋል።

በሃይቆቹ ላይ የተከሰተውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከአካባቢ መስተዳድሮች፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ  አካባቢ የሚገኘውን የሎጎ ሐይቅን ከተጋረጠበት የመጥፋተ አደጋ ለመታደግ ከሁለት ዓመት በፊት ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተጀመሩት የጥናትና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን በማሳያነት አቅርበዋል።

በሎጎ ሀይቅ አካባቢ ያለው የእርሻ አጠቃቀም ክፍተት ሀይቁን በደለል እንዲሞላ ማድረጉ፣ የመጤ አረም መከሰትና መስፋፋት እንዲሁም ህገወጥ አሳ ማስገር ለሀይቁ የመጥፋት አደጋ ተጋላጭነት ምክንያቶች እንደሆኑ በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰዋል ።

"ሀይቁን ለመጥፋት አደጋ ያጋለጡ ችግሮችን ለመፍታት  ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር እንሰራለን" ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩን ያሳተፈ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማካሄድ፣ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል፣ በሃይቁ አካባቢ ትላልቅ የጎርፍ መከላከያ ግድቦችን ለመገንባት ባለስልጣኑ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሃይቁ ዙሪያ የሚካሄደውን የሰብል ልማት በማስቀረት አርሶ አደሩ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የሃይቁን ደህንነት በመጠበቅ ተጣቀሚ እንዲሆን ለማስቻል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።

የሎጎ ሐይቅ እየቀነሰ ሲሄድ አርሶአደሮች እየተከተሉ የማረስ ልምድ እየጨመረ መምጣት ለሀይቁ የመጥፋት ተጋላጭነት ዋና ምክንያት  እንደሆነ በጥናት መታወቁን የገለጹት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ኃይሉ ናቸው።

"በአካባቢው የእርሻ መስፋፋት በተለያየ አቅጣጫ ወደ ሀይቁ ደለል እንዲገባ በማድረግ  የሃይቁ ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ እንዳደረገው በጥናት ተደርሶበታል" ብለዋል ።

በባለስልጣኑ ሀይቁን ለመታደግ እያደረገ ባለው ጥረት ዩኒቨርሲቲው በግንባር ቀደም እየተሳተፈ መሆኑን አስታውቀዋል ።

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሀብት መምህር ዶክተር ሐሰን መሃመድ "የሎጎ ሐይቅ ከየት ወደ የት" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት  ሀይቁ 2 ሺህ 205 ሄክታር ስፋትና 88 ሜትር ጥልቀት እንደ ነበረው አመልክተዋል፡፡

ሀይቁ ባለፉት ዓመታት ባጋጠመው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ጥልቀቱ ወደ 81 ሜትር መቀነሱን ጠቁመው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በደለል የመሞላት ፍጥነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደረገው መሆኑን ጠቁመዋል።፡

"በውሃ ተሸፍኖ የነበረው የሃይቁ አካልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሸሸ እየመጣ ነው" ያሉት  ዶክተር ሐሰን የተጠናከረ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማካሄድና ከከተማ ወጥቶ ወደ ሀይቁ የሚገባን ቆሻሻ በማስቀረት አደጋውን ለመቀልበስ እንደሚቻል በመፍትሄነት አመላክተዋል፡፡

የተሁለደሬ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ አለልኝ ሐይቁን በሚያዋስኑ ወረባቦና ሐይቅ ከተማ ጭምር  ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተጠናከረ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሃይቁን ደህንነት ለመጠበቅ በተያዘ አቅጣጫ መሰረት ባለፈው ክረምት ብቻ ከ120 ሺህ በላይ የፍራፍሬ ችግኞች በሀይቁ ዙሪያ ባሉ ማሳዎች መተከላቸውን ጠቅሰዋል።

በሀይቁ አቅራቢያ ለሰብል ልማት ይገለገሉበት በነበረው ማሳቸው ላይ ባለፈው ክረምት  ከ300 በላይ የማንጎና የአቡካዶ ችግኞችን በመትከል የሃይቁን ደህንነት ለመጠበቅ እየተጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በተሁለደሬ ወረዳ የቀበሌ 017 ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ መሃመድ ናቸው።

በሀይቅ ከተማ ከትላንት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ የባለስልጣኑ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የስራ ኅላፊዎችና የዘርፉ ምሁራን፣ የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም