የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያ ሲገቡ በቀላሉ ቪዛ የሚያገኙበት አሰራር መመቻቸቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያ ሲገቡ በቀላሉ ቪዛ የሚያገኙበት አሰራር መመቻቸቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 06/2013 (ኢዜአ) የውጭ አገሮች ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በቀላሉ ቪዛ የሚያገኙበት አሰራር ማመቻቸቱን ቱሪዝም ኢትዮጵያ ገለፀ።
የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ በመላው ዓለም ስጋት መፍጠሩን ተከትሎ ከተጎዱት ዘርፎች መካከል ቀዳሚው የቱሪዝም ዘርፍ ሲሆን፤ የሰዎች እንቅስቃሴ በመገደቡ ቱሪዝም ከፍተኛ መቀዛቀዝ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጤና ሚኒስቴር የወረርሽኙን ስርጭት መቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ስራቸውን እንዲቀጥሉ በሰጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደተለያዩ አገሮች የሚያደርገውን በራራ እንደገና በመጀመሩ የቱሪዝም ዘርፉ የማነቃቂያ ፓኬጅ አዘጋጅቶ ባለፈው ጥቅምት ወር ወደ ስራ ገብቷል፡፡
የቱሪዝም ኢትዮጵያ የኮንቬንሽን ቢሮ ዳይሬክተር አለማየሁ ገብረትንሳይ "ሁሉም የአፍሪካ አገሮችና ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ዓለም አገሮች ዜጎች ኢትዮጵያ ሲደርሱ ቦሌ አየር ማረፊያ ላይ የመዳረሻ ቪዛ የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷል" ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የቪዛ ፎርም መሙላት የሚፈልጉ ጎብኚዎች ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የኢ-ቪዛ ስርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል፡፡
የጎብኚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ በተለያዩ አገሮች እንዳለው የቱሪስት ፖሊስ በኢትዮጵያ እንዲደራጅ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ምክረ ሃሳብ ሲያቀርብ መቆየቱን አቶ አለማየሁ አስታውሰዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ አገልግሎቱን ሲያደራጅ የቱሪስት ፖሊስ ሁኔታን ከግምት በማስገባት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
“አደረጃጀቱ የሰው ኃይል ተሟልቶለት ወደ ተግባር ሲገባ ቱሪስቶች በየትኛው አካባቢ ያለ ስጋት መንቀሳቀስ ይችላሉ” ነው ያሉት።
የቱሪስት ፖሊስ ተደራጅቶ የሰዉ ሀይሉ ሲመደብ የቱሪስቶችን ጸጥታና ደህንነት ማስከበር እንደሚቻል ገልጸዋል።