ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ ከሉሲ በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውን አትሌቲክስ በአግባቡ መጠቀም ይገባል - ዶክተር ሒሩት ካሳው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ ከሉሲ በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውን አትሌቲክስ በአግባቡ መጠቀም ይገባል - ዶክተር ሒሩት ካሳው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ ከሉሲ በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውን አትሌቲክስ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 24ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።
ጉባዔው ፌዴሬሽኑን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትነት የሚመሩ ግለሰቦችን መርጧል።
በ2012 ዓ.ም የፌዴሬሽኑ የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና በ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይም ተወያይቷል፤ የ2012 ዓ.ም የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርቱን በመመርመርም በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው በጉባዔው መክፈቻ ንግግራቸው አትሌቲክስ ኢትዮጵያን በዓለም በማስተዋወቅ ከሉሲ በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል ብለዋል።
በመሆኑም አትሌቲክሱን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ዘርፉ "ምንጭ ሳይሆን ሰፊ ባሕር ነው" በማለት አገራዊ ጥቅሙን አጉልተው አሳይተዋል።
ፌዴሬሽኑ ይህን ሰፊ ባሕር ለመጠቀም ከባለሙያዎች፣ ከክልሎችና ከክለቦች ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትነት ሃላፊነቱ ከለቀቀበት ከሕዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ፌዴሬሽኑን በተቀዳሚ ፕሬዚዳንትነት በበላይነት ስትመራ ቆይታለች።
በመሆኑም ጠቅላላ ጉባዔው ለመጪዎቹ አራት ዓመታትም ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እንድትመራ መርጧታል።
የጉባኤው አባላት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱን ከመረጡ በኋላ ፌዴሬሽኑን የሚመሩ ስምንት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጠዋል።
ለቀጣዩቹ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን እንዲመሩ ከተመረጡት ስራ አስፈጻሚዎች መካከል የሴቶች ድርሻ 60 በመቶውን ይዟል።
ስራ አስፈጻሚዎቹ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ አቶ በላይነህ ክንዴ፣ ዶክተር በዛብህ ወልዴ፣ አቶ ተፈራ ሞላ፣ ወይዘሮ ትልቅሰው ገዳሙ ፣ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ፣ ወይዘሮ ፎዚያ እንድሪስና ወይዘሮ ሳራ ሃሰን ናቸው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ባለፈው ዓመት ባሳዩት የስራ አፈፃፀም መሰረት ከ20 ሺህ እስከ 240 ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል።
በተመሳሳይ ክለቦች በ2012 ዓ.ም ለነበራቸው አፈጻጸም ከ40 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር ሸልሟል።