ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገልግሎት ጥራቱን በማሻሻል ተወዳዳሪነቱን ሊያሳድግ ይገባል -ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ተወዳዳሪነቱን ሊያሳድግ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ ገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባንኩን የሩብ አመት አፈጻጸምና አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከት ውይይት አድርጓል።     

በውይይቱ ላይ ባንኩ በአዳዲስ ሂሳብ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና ብድር አገልግሎቶች ላይ ያከናወናቸውን ተግባራትና አፈጻጸም አቅርቦ ተገምግሟል።   

የባንኩ እቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ መሸሻ ደሜ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባንኩ በሩብ ዓመቱ ከግሉ ዘርፍ 9 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ አቅዶ ነበር።

 ሆኖም  ከታቀደው  ከአራት እጥፍ ብልጫ ያለው 38 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን ተናግረዋል።      

ከዚሀም 51 በመቶ የቁጠባ ድርሻ ሲሆን፣ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ደግሞ 41 በመቶ እንደሚይዝ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

እንደ አቶ መሸሻ ገለጻ በሩብ ዓመቱ 796 ሺህ ተጨማሪ አካውንቶች የተከፈቱ ሲሆን፣ ይህም በባንኩ ውስጥ ያለውን አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ከፍ አድርጎታል።    

አፈጻጸሙ የተሻሻለው የባንኩን ዘርፍ የሚያነቃቁ አሰራሮች በመዘርጋታቸው፣የብር ኖት ለውጥ መደረጉና የባንኩን አሰራር ወደ ደጂታል ለማስገባት በመሰራቱ ነው ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በአገሪቷ የባንኮች ቁጥር እየጨመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።  

ቅርጫፎችን በማስፋፋት በተለይም በአርሶ አደሩ ተደራሽ ለመሆን ጠንክሮ እንዲሰራም አስገንዝበዋል።   

የኤ ቲ ኤም ማሽኖች በአግባቡ አገልግሎት ያለመስጠት፣ እንዲሁም በባእላትና ቅዳሜና እሁድ ገንዘብ የማይኖራቸው ማሽኖች መኖራቸውን ያነሱት አባላቱ ይህም በቀጣይ እንዲስተካከል አጽንኦት ሰጥተዋል።  

በተለይም ለደንበኞች አገልግሎት የሚሰጡ  መስኮቶች ውሱንነት የሚፈጥረውን የአገልግሎት መስተጎጓል  እንዲያስተካክል ነው የምክር ቤቱ አባላት ያሳሰቡት።  

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተወካይ ወይዘሮ ሳራ አቢ ባንኩ ከወለድ ነጻ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ሚና ሊጫወት ይገባል ብለዋል።    

ከሰራተኞች ጋር በመነጋገርና ተገቢውን አቅጣጫ በመስጠት የባንኩን አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እንዲሰራም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍቅረስላሴ ዘውዱ ባንኩ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ለሰራተኞች የክህሎት ስልጠና እንደሚሰጥና የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች እንደሚያከናውን ተናግረዋል።   

ባንኩ ደንበኞች የሚስተናገዱበት በቂ ቦታና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የደንበኞች ቅሬታና አስተያየት ማስተናገጃ ስርዓት መዘርጋቱን አስታውቀዋል።

ከኤቲ ኤም ማሽን ጋር በተያያዘም በአሁኑ ወቅት ካሉት 3 ሺህ ማሽኖች ውስጥ 86 በመቶ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስረድተዋል።  

የባንኩን ቅርጫፎች ለማስፋፋት በተለይም 170 የወረዳ ከተሞች መለየታቸውን አንስተው፣ በቀጣይም ተደራሽነትን ለማስፋት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።  

የባንኩ ከወለድ ነጻ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ኑሪ ሁሴን በበኩላቸው በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት 57 ቅርንጫፎች ከወለድ ነጻ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አገልግሎቱን ለማስፋትና ተጨማሪ ቅርጫፎችን ለመክፈት በጥናት የተደገፈ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቢ ሳኖ በበኩላቸው ባንኩ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም