ቀጥታ፡

በኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ብልሹ አሰራሮችና ከመመሪያ ውጭ ህገ ወጥ ተግባራት መፈጸማቸው ተገለጸ

አዲስ አባባ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) በኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ብልሹ አሰራሮችና ከመመሪያ ውጭ የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት መፈጸማቸውንና የፌዴራል ኦዲት ግኝትም ይህንኑ እንደሚያሳይ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ2011 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ላይ አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበው የ2011 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል።

በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ብልሹ አሰራሮች መታየታቸውንና ከመመሪያ ውጭ የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት መፈጸማቸውን የፌዴራል ኦዲት ግኝት እንደሚያሳይ ተገልጿል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሶስት ዓመታት ያልተስተካከለ ተመሳሳይ የኦዲት ግኝት መገኘቱን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአንድ ቀን አንድ ሰው ሁለት ቦታዎች እንደሄደ በመጥቀስ አበል እንደተከፈለ የሚያሳይ የኦዲት ግኝት መገኘቱን ገልጸው አሰራሩ ሊታረም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በተቋሙ የአበል መክፈያ ቅጽ ሳይኖር አበል እንደተከፈለና ዩኒቨርሲቲው ይህንኑ በማጣራት ህገ ወጥ ተግባሩን በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የፋይናስ አሰራርን ብልሹነት በተቋሙ በመታየቱ በቀጣይ ትኩረት በመስጠት የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተገቢ ያልሆነ የአበል አከፋፈሉን ማስቀረትና ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያን በመንግስት አሰራር መሰረት መተግበር እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ዮሱፍ አሳስበዋል።

ለአብነትም ዩኒቨርሲቲው ከተለያየ ገቢ የሰበሰበውን 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉን የኦዲት ግኝቱ እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረባቸውን ክፍያዎች በተገቢው መዝገብ በመያዝ ለሚመለከተው አካል ገቢ አለማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

በዚህም 205 ሺህ ብር የጉዳት ካሳ ከተለያዩ ድርጅቶች ማስመለስ አለመቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ህግና ደንብን ሳይከተል ለተለያዩ ሰራተኞች 490 ሺህ ብር የትርፍ ሰዓት ክፍያና 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የውሎ አበል ክፍያ መፈጸሙን የዋና ኦዲተር ሪፖርት ማሳየቱንና ይህም የህዝብ ኃብት ያለአግባብ እንዲባክን ማድረጉን ተናግረዋል።

የዋጋ ማወዳደሪያ ሳይቀርብ ከተመሳሳይ ማህበራት የ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግዥ መከናወኑንና 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ግዥዎችን ከውድድር ውጭ መፈጸማቸውን በኦዲት ግኝት ተረጋግጧል።

በተቋሙ የሚታየውን የሰው ኃይል ፍልሰት ማስቀረትና ፣ተጠያቂነትን መሰረት ያደረገ አሰራር መከተል እንዳለበትም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቁመዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሙክታር መሀመድ በፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ ሰራተኞች በተደጋጋሚ ስራ መልቀቅ፣ ከአዳዲስ ሶፍትዌሮች ጋር በደንብ ያለመተዋወቅ ፣ የመረጃ አያያዝ ችግሮች ለኦዲት ግኝቱ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል።

የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን ተከትሎ ላሉት ሰራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ በመክፈል ለመስራት መሞኮሩንና ፣ የተወሰኑ የትራንስፖርት ማህበራት በጭሮ ከተማ በመገኘታቸው ለተማሪዎች የመስክ ስራ አገልግሎት በኪራይ ተጠቅመናል በማለት ፕሬዝዳንቱ ምላሽ ሰጥተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን ግብረ መልስ መቀበላቸውንና በቀጣይ የኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም