ቀጥታ፡

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመዲናዋ ነዋሪዎች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በመዲናዋ ለሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ሥራዎች ለሚያደርጉት ድጋፍ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ምስጋና አቀረቡ፤ ነዋሪዎቹ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጠይቀዋል።

ጃን ሜዳን ለሃይማኖታዊ በዓል በሚመጥን መልኩ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ እንደሆነም ገልፀዋል።

ምክትል ከንቲባዋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩን የተለያዩ ሥራዎች ሲያግዙ ቆይቷል።

በተለይም መከላከያ ሠራዊት ለኅዝብ ሰላም፣ ደህንነት አብሮነት ለከፈለው መስዋዕትነት የደረሰበት ጥቃት የከተማዋን ነዋሪዎች ያስቆጣና በጋራ ያቆመ መሆኑን ገልጸዋል።

መከላከያ ሠራዊት "ራሱ እየሞተ እኛን ያኖረ ሠራዊት ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ የተፈጸመበት ጥቃት "እጅግ በጣም አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር ነው" ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ የመዲናዋ ነዋሪዎች ካደረጉት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በላይ ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አክብሮት አሳይተዋል ነው ያሉት።

ለአብነትም በአንድ ሳምንት ውስጥ ለመከላከያ ሠራዊት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉ የከተማ አስተዳደሩ በአድንቆት የሚመለከተው መሆኑን አንስተዋል።

ጎን ለጎንም ኅብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ አጋር እንደነበር ገልጸው በየቀኑ ከሚደርሱት ጥቆማዎችም 98 በመቶዎቹ ትክክለኛ ጥቆማዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪ ኮቪድ 19ን መከላከል፣ ለተማሪዎች ምገባ፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብና ለሌሎችም በጎ ተግባራት በጥቂት ወራት ውስጥ በድምሩ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

"የአዲስ አበባ ነዋሪ በጣም ተባባሪና አስተዋይ ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ድጋፉን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል ብቻ የሚከበርበት ሳይሆን ሌሎችም በርካታ ማኅበራዊ ኩነቶች የሚካሄዱበት በመሆኑ በዚህ ደረጃ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁንም የጥምቀት በዓል እየተቃረበ በመሆኑ ሥፍራውን ለሃይማኖታዊ በዓሉ በሚመጥን መልኩ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሥፋራው በጊዜያዊነት ተዘዋውረው የቆዩ ነጋዴዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ የሚሰሩበት የገበያ ማዕከል ተገንብቶ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሥፍራው ሁሉንም የገበያ ተዋናይ፤ የግብዓት አቅራቢንም ጭምር ማዕከል ያደረገና ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል መሆኑን አስረድተዋል።

የአትክልት ተራ ነጋዴዎችም ማፍረስና ማጽዳት ይጀመራል ከተባለበት ቀናት በፊት ሥራዎችን ከወዲሁ እያጠናቀቁ መሆኑን አንስተው፤ ለነጋዴዎቹ ምስጋና አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ከ1 ሺህ 400 በላይ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ፣ ሱቆችና ሌሎች አገልግሎቶችን መሥጠት የሚችለው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል። 

ፕሮጀክቱ ማንኛውም ግለሰብ ስለከተማዋ ለማወቅ፣ በከተማዋ የት መጎብኘት እንደሚችልና ስለመዲናዋ እድገት አስተያየት መሥጠት የሚችልበት ማዕከልም እንዳለው ጠቁመዋል። 

ከመስቀል አደባባይ በቸርችል አድርጎ እስከ ማዘጋጃ ቤት እየተሰራ ያለው የመንገድ ውበት ነው፤ በቅርቡ ይጠናቀቃል ነው ያሉት። 

የፈጣን አውቶብስ አገልግሎት ፕሮጀከት የመዘርጋት ሥራ እንደተካተተበት ጠቅሰው ሌሎችም የመሰረተ-ልማት ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ የወደፊቷን አዲስ አበባ ታስቦ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል።

ለመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት አስተባባሪዎችና ሰራተኞች ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ላሳዩት ቁርጠኝነትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም