ረቂቅ አዋጁ በሙያው የዳበረ ሚዲያ ለመገንባትና የፕሬስ ነጻነትን ለማረጋገጥ መልካም ዕድል ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ አዋጁ በሙያው የዳበረ ሚዲያ ለመገንባትና የፕሬስ ነጻነትን ለማረጋገጥ መልካም ዕድል ይፈጥራል
አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ በሙያው የዳበረ ሚዲያ ለመገንባት፣ የፕሬስ ነጻነትን ለማረጋገጥና አቅማቸውንም ለማጎልበት መልካም ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ተገለጸ።
ነጻ ገለልተኛና ለዴሞክራሲ ሽግግሩ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መገናኛ ብዙሃንን ለማጠናከር አይነተኛ ሚና ይጫወታልም ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይፀድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመራው አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ ከስያሜ ለውጥ ጀምሮ ተጠሪነቱንም በቀጥታ ለምክር ቤቱ ያደረገ ሆኗል።
ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በሚል ዳግም ለሚቋቋመው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ህጋዊ ኃላፊነት የሚያጎናጽፍ ነው።
ሁሉም ሚዲያዎች በጋራና በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙ በሚዲያ ፖሊሲውም ሆነ በረቂቅ አዋጁ የተደነገገ ከመሆኑ አንጻር ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንደሚያበረክት ታምኖበታል።
ኢዜአ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጁ ምን አንኳር ጉዳዮችን አካቷል? ሲል ጠይቋል።
የአዋጁ አርቃቂ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ጎሹ ስራ ላይ ያለው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መገናኛ ብዙሃን ነጻና ገለልተኛ ሆነው በራሳቸው እንዲሰሩ የማይመችና የሕግ አተገባበር ክፍተቶችም ያሉበት ነው ይላሉ።
ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትና የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ በሚል የተሻሻለው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በሚዲያው ዘርፍ የነበሩ የሕግ ክፍተቶችን የሚቀርፍና አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በተቋም ደረጃም የአሰራር ነጻነታቸው ተጠብቆ ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲሰሩና አቅማቸው እንዲጠናከር በማስቻል ረገድም ረቂቅ አዋጁ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።
በሌላ በኩል መገናኛ ብዙሃኑ ሲያጠፉ እንደ ጥፋታቸው መጠን የአስተዳደርና የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው የሚደነግግ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ረቂቅ አዋጁ ለባለስልጣኑም ሆነ ለመገናኛ ብዙሃን ባለድርሻ አካላት እመርታዊ ለውጦችን የሚያመጣ መሆኑን ገልጿል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም በሥራ ላይ ያለው የብሮድካስት አዋጅ የወቅቱን የሚዲያ ነባራዊ ሁናቴ የዋጀ አይደለም ይላሉ።
ለዚህም ሁሉንም የሚዲያ አይነቶች ያላካተተ፣ የብሮድካስት ባለስልጣን ተጠሪነትን ለማስታወቂያ ሚኒስቴር በሚል የደነገገና የበይነ መረብ ሚዲያን ያላካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የበይነ መረብ ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ ከበጎ ዕድሉ ባሻገር አገራዊ ጉዳቶችም እንዳሉት ጠቁመው በአዲሱ አዋጅ የበይነ መረብ ሚዲያን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ለባለስልጣኑ ስልጣን መሰጠቱን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል አዲሱ አዋጅ ለሚዲያው ዘርፈ ብዙ በረከቶችን ይዞ ስለመምጣቱ አብራርተዋል።
በውጭ አገር የሚኖሩ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የሃይማኖት ተቋማት በሚዲያ ዘርፍ እንዳይሳተፉ የሚከለክለው ድንጋጌ መነሳቱን ተከትሎ እውቀትና ልምዳቸውን ተጠቅመው በዘርፉ እንዲሰማሩ የሚያስችል መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በመጽሔትና ጋዜጣ ባለቤትነት በግልም ሆነ በማኅበር ማቋቋም እንደሚቻል መፍቀዱ ለሚዲያው ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መስፋፋትና ጥራት የተሻለ ሁናቴ እንደሚፈጥር ይጠበቃል ብለዋል።
አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ በሙያው የዳበረ ሚዲያ ለመገንባት፣ የፕሬስ ነጻነትን ለማረጋገጥ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድም የሚዲያ ግንዛቤን ለማጎልበትና አቅም ለመገንባት መልካም ዕድል ይዞ እንድሚመጣ ታምኖበታል።
የሚዲያውን አቅም መገንባት፣ መደገፍና መከታተል የሚያስችል አደረጃጀት ያለው ከመሆኑ አንጻር አዋጁ ለመገናኛ ብዙሃን ባለድርሻ አካላት በሙሉ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ እንደሆነ ነው የተገለጸው።
አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ገቢራዊ ከተደረገ መገናኛ ብዙሃን የሚደጋገፉበትና በይዘት የሚጠናከሩበት ስርዓት እንዲዳብር የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ተጠቁሟል።