ቀጥታ፡

ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ሂደት የስነ-ልቦና ድጋፍ ማድረግ ይገባል --የሥነ-አእምሮ ህክምና ስነ ልቦና ባለሙያዎች

ድሬዳዋ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ወደ ቀደመ አኗኗራቸው ለመመለስ በሚከናወኑ ተግባርራት ውስጥ ለተጎጂዎች የሥነ-ልቦና ጉዳይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የሥነ-አእምሮ ህክምና ስነ ልቦና ባለሙያዎች አስታወቁ።

"መፈናቀል ለደረሰባቸው ተጎጂዎች ከቁሶች በላይ የሥነ-ልቦና ድጋፍ ማድረግ ወደ ቀድሞ አኗኗራቸው ፈጥነው እንዲመለሱ ያግዛቸዋል" ሲሉም ባለሙያዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ 

የድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል የሥነ-አእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ፂዮን ደበበ እንደተናገሩት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በደረሱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ ለሥነ-አእምሮ ጤናና ለሥነ-ልቦና ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በተለይም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የህወሃት ጁንታ ቡድን መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከተሎ መንግስት ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻ የገባበትን ሁኔታ ጠቅሰዋል።

"ክስተቱን ተከትሎ በአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳዮች የተጎዱና የተፈናቀሉ ዜጎች ለጭንቀት፣ ለፍርሃትና ለተስፋ መቁረጥ ሊጋለጡ ይችላሉ" ብለዋል፡፡

መንግስት በህግ ማስከበር ሥራው ወቅት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገው ጥረት የሚደገፍ መሆኑን ጠቁመው ተጎጅዎችን መልሶ በማቋቋም ሂደት ውስጥ ዜጎች ከገቡበት የሥነ-ልቦናዊ ጫና እንዲለቀቁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ  አመላክተዋል፡፡

ተጎጂዎች ከገቡበት የሥነ ልቦና ጫና እንዲላቀቁ በፍጥነት ካልተሰራ ለሥነ አእምሮ ጤና ችግር ሊዳረጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚያደረገው ጥረት ውስጥ የሥነ-አእምሮ ጤናና የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባው ዶክተር  ፂዮን አመላክተዋል፡፡

"በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት ችግሩ በደረሰባቸው አካባቢዎች ከሚኖሩ ዜጎች አብዛኛዎቹ ለሥነ-አእምሮ ጤናና ለሥነ-ልቦና ችግር ይጋለጣሉ" ያሉት ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር አልሙሳ ጊፖ ናቸው።

"በዚህ ጊዜ በችግሩ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ተረጋግተው የማሰብና ነገሮችን የማከናወን ችግር ስለሚያጋጥማቸው ለተጎጂዎች ተገቢው የስነ-ልቡና ድጋፍ በወቅቱ ማድረግ ለቀጣይ ሕይወታቸው መስተካከል ወሳኝ ነው" ብለዋል።

"ባደጉት ሀገራት መሰል ክስተቶች ሲገጥሙ ከህክምናና ከሥነ-ልቡና ተቋማት ጋር ተባብሮ መሥራት የተለመደ ነው " ሲሉም  ተሞክሮውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከሥነ ልቦና ድጋፉ ጎን ለጎን ህዝቡ ለዘመናት ያዳበረውን የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴት በማጠናከር ተጎጂዎችን አለንላችሁ ሊል እንደሚገባ አመላክተዋል።

"የኀብረተሰቡም ያለንላችሁ ድጋፍ ተጎጂዎችን ተስፋ እንዲሰንቁና መልሰው በመቋቋም ሂደት ውስጥ ፈጥነው እንዲያገግሙ ያግዛቸዋል "ብለዋል፡፡

በአፋር ክልል በክረምት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ወቅት ኀብረተሰቡ ከጫፍ ጫፍ ያሳየው ድጋፍና የወንድማማችነትን ስሜት በችግሩ የተጎዳውን ህዝብ ሥነ-ልቦና ለማከም ያደረገውን አስተዋፆ  ፕሮፌሰር አልሙሳ ለአብነት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም