ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎበኙ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎብኝተዋል።
ምክትል ከንቲባዋ በጉብኝታቸው የሚዲያ ኮምፕሌክሱ በውስጡ የያዛቸውን የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ተመልክተዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት አስተያየት ኢዜአ ያስገነባው አዲስ የሚዲያ ኮፕሌክስ ለከተማውም ሆነ አጠቃላይ ለአገሪቷ የሚዲያ እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢዜአ በዚህ መልኩ አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ማደራጀቱ ተቋሙ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የተቋሙ አጠቃላይ ዝግጅት ለሌሎች የሚዲያ ተቋማትም በአርዓያነት ሊወሰድ የሚችል ተሞክሮ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ መሬት እንዲለማ ካለው ፍላጎት አኳያ ኢዜአ በአጭር ጊዜ በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረጉ እና የከተማዋ ገጽታ እንዲቀየር በማድረጉም ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ እስካሁንም ከኢዜአ ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ወደ ፊትም በትብብርና በአብሮነት እንደሚዘልቅ አረጋግጠዋል።
የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና በውስጡ 3 የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎች፣ 4 የሬዲዮ ስቱዲዮዎች፣ በርካታ የኤዲቲንግ ክፍሎችን ጨምሮ ጂም፣ ላውንደሪ፣ ሳውና ባዝ፣ ላይብረሪ አና ልዩ ልዩ መዝናኛዎችን ያካተተ ነው።
ለህንጻው ግንባታ አጠቃላይ 161 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።