በቤልጅየምና ሉክሰምበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ለተቸገሩ ወገኖች ከ312 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በቤልጅየምና ሉክሰምበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ለተቸገሩ ወገኖች ከ312 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) በቤልጂየምና ሉክሰምበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ለተቸገሩ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ከ312 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።
በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበይነ መረብ ያዘጋጀው የሰብአዊ ድጋፍ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርና ውይይት ትናንት ተካሄዷል።
በቤልጂየምና በሉክሰምበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች፤ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ ድጋፍ ዓላማ በተከፈቱት የሂሳብ ቁጥር በቀጥታ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በዕለቱ 82 ሺህ 483 ብር ገቢ መደረጉን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ በፊት የተደረገውን 229 ሺህ 617 ብር ድጋፍ ጨምሮ በሁለቱ አገራት የሚገኙት ዳያስፖራዎች በአጠቃላይ 312 ሺህ 100 ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ 507 ሺህ 800 ብር ለመስጠት ቃል መገባቱም ተመልክቷል።
በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ፤ በትግራይ ክልል የተፈናቀሉትንና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም መንግስት ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊውያን መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
ለወገን ደራሽ ወገን ነው ያሉት አምባሳደር ሂሩት ለተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍን እንደሚሹ አብራርተዋል።
በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የሰብአዊ ድጋፍ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በጋራ በመሆን በበይነ መረብ አማካኝነት የድጋፍ ማሰባሰቡ እና ቃል የመግባት ሂደት ከተጠበቀው በላይ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል ብለዋል።
ለሰብአዊ ድጋፉ አስተዋጽኦ ላደረጉት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴው የገንዘብ እና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ በማሰባሰብ እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ አምባሳደር ሂሩት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የተደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያዊያን ለወገኖቻቸው ያላቸውን ፍቅር የገለጹበት እንደሆነና በቀጣይም የድጋፍ ማሰባሰብ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የኮሚኒቲ አደረጃጀት ተወካዮች የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው ወገኖች ድጋፍ ማድረግ መቻል የኢትዮጵያዊነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ክብርም ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል።
ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉና በቀጣይም ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ING- BE 62363121484961 -BIC-BBRUBEBB,communication-social support፣GOFUNDME https://www.gofundme. com /f/social-support-for-humanitarian-aid-ethiopia እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000354217019 በባንኩ ስዊፍት ኮድ CBETETAA ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ኤምባሲው ገልጿል።
በቤልጂየም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቤልጂየም፣ሉክሰምበርግና የአውሮፓ ሕብረትን የሚሸፍን ነው።