ቀጥታ፡

የልዩ ዘመቻዎች ኃይል የታገቱ ወገኖችን ከጁንታው እጅ ፈልቅቆ በማውጣት ለሠራዊቱ አባላት ጭምር መከታ መሆኑ ተመለከተ

ሀዋሳ፤ ታኅሳስ 5/2013 (ኢዜአ) የልዩ ዘመቻዎች ኃይል በየቦታው ፈጥኖ በመድረስ የታፈኑና የታገቱ ወገኖችን ከሰው በላው ጁንታ እጅ ፈልቅቆ በማውጣት ለሠራዊቱ ጋሻና መከታ መሆኑን አስመስክሯል ሲሉ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ አስታወቁ።

በቀጣይም ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመፈፀም በተሟላ ቁመና ላይ እንደሚገኝም  አስታውቀዋል።

ሜጀር ጄኔራል ሹማ ለኢዜአ እንደገለፁት በቀቢፀ  ተስፋ የተዋጠው ጥገኛ  የህወሓት  ቡድን በሰሜን የነበረውን የሀገር ሠራዊት በተለያየ  መንገድ  ሲተናኮል  ቆይቶ  ባልታሰበ  ሰዓትና ወቅት ታሪክ ይቅር የማይለው ጥቃት ፈፅሟል።

"ጁንታው በተለይ ሠራዊቱን ለመጨፍጨፍ በውስጣችን የመሸጉ  የጅብ ግልገሎችን  በመጠቀም በሰሜን ዕዝ ሠራዊታችን ላይ ከበባ በፈፀመበት ወቅት የልዩ ዘመቻዎች  ሠራዊት አባላት ከደቡብ ፈጥኖ በመነሳት ታድጓል" ብለዋል።

ሌሎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክፍሎቻችን እስከሚደርሱ ድረስ የልዩ ዘመቻዎች  አባላት ከጎንደር ሶራቃ በመነሳት የጠላትን ምሽግ እየደረመሰ በዳንሻ ተከበው የነበሩ የአምስተኛ ሜካናይዝድ አመራሮችና ሠራዊት አባላትን ከነትጥቃቸው ጭምር ከከበባ በማውጣት ለወገን ፈጥኖ ደራሽነቱን በተግባር ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

በጁንታው ጥቃት ኤርትራ የገቡ የሰሜን ዕዝ አባላት ተደራጅተው በአጭር ጊዜ በጠላት ላይ ድል እንዲያገኙ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል አባላት ሚና የላቀ እንደነበርም ገልፀዋል።

"በአጠቃላይ ክፍሉ በየቦታው ፈጥኖ በመድረስ ለጠላት ውጋት ለወገን ደግሞ ኃይልና ብርታት መሆኑን አሳይቷል" ብለዋል።

"ሠራዊቱ ያልተሳተፈበት ግንባር የለም" ያሉት ሜጀር ጀነራሉ በተለይ ተደራጅተው ከደረሱ ሌሎች እግረኞች ጋር በመቀናጀት በዛላንበሳ በኩል የጠላትን ምሽግ በመናድና ጠላትን በመደምሰስ የማይበገር ክንደ ብርቱነቱን እስከ መቀሌ ድረስ በማሳየት አኩሪ ገድል መፈጸሙን አስረድተዋል።

ህግ በማስከበር ዘመቻው አንድም ሲቪል ዜጋ ላይ ጉዳት እንዳይደረስ የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ጠላትን ከከተማ በማስወጣት መደቆስ መቻሉን ሜጀር ጄነራል ሹማ አብራርተዋል።

በአጠቃላይ የሠራዊቱ አባላት ያገኘውን ወታደራዊ ስልጠና በግዳጅ ላይ ለመተርጎም ያሳየው ቁርጠኝነት፣ ጀግንነትና ሀገራዊ ፍቅር ጥንቃቄ በተሞላበት መንፈስ ማጠናቀቁን  አረጋግጠዋል።

ህግ የማስከበር ዘመቻው በአነስተኛ ኪሳራና በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀ በመሆኑ በቀጣይ ለማንኛውም ግዳጅ ብቃቱም ኃይሉም የተሟላ መሆኑን ሜጀር ጀኔራል ሹማ አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ “ንስር” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ንስር ብልጥ፣ጠንቃቃ፣አላማውንና ፍላጎቱን በሚገባ ሊያሳካ የሚችል የጀግና መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

"ልዩ ዘመቻውን የሚመራው ጦርም ኮማንዶ፣ ልዩ ኃይል፣ አየር ወለድ ስለሆነ  ተፈጥሮና  ሰው ሰራሽ አደጋ ሳያግደው የሚሰጠውን ማንኛውንም ግዳጅ የሚፈፅም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እኔም ይህንን ጦር ስለምመራ በጦሩ ስም የተሰጠኝ ስያሜ ነው" ብለዋል።

በብላቴ የሚገኘው የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ለ33ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የሪፐብሊካን ጋርድ መሠረታዊ ኮማንዶ አባላትን ትላንት ማስመረቁን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም