ሠራዊቱ ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ግዳጁን ፈፅሞ በቅርቡ ወደ መደበኛ ስራው ይመለሳል - ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ግዳጁን ፈፅሞ በቅርቡ ወደ መደበኛ ስራው ይመለሳል - ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) ሠራዊቱ ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብና ሌሎች ግዳጆችን አጠናቆ በቅርቡ ወደ መደበኛ ስራው እንደሚመለስ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ጀነራሉ የህወሓት ጁንታን በገዥነትና በትምክህት የክህደት ጫፍ ላይ በመድረስ ሕዝብ ሲያገለግሉ የነበሩና የአብራኩ ክፋይ የሆኑ የሠራዊት አባላትን 'የበላ አሸባሪ ሃይል ነው' ሲሉ ገልፀውታል።
ጁንታው ለዓመታት የጥፋት ሴራ በመሸረብና ሃይል በማሰባሰብ የተዘጋጀ ቢሆንም በሠራዊቱና በሕዝቡ ላይ የፈፀመው የክህደት ግፍ ጥሎታል ነው ያሉት።
'ጦርነቱ በሣምንታት ያልቃል ብሎ የገመተ አልነበረም' ያሉት ኢታማዦር ሹሙ ሃቅና ፍትህ ስላለን በአጭር ጊኤ ጁንታውን ላይመለስ መደምሰስ ተችሏል ብለዋል።
በመከላከያ ሠራዊት ጀግንነት የትግራይና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገላግሏል ነው ያሉት።
መከላከያ ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት የመንግስትን የመልሶ ማቋቋም ስራ የመደገፍና መደበኛ የፖሊስና የትራፊክ አገልግሎቶች እንዲስተካከሉ የማገዝ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጀነራል ብርሃኑ ሠራዊቱ የተበታተኑ የጁንታው አባላትን ለሕግ የማቅረብ ስራውን እያከናወነ መሆኑንና በቅርቡም ተልዕኮውን ጨርሶ ወደ መደበኛ ስራው እንደሚመለስ ገልፀዋል።