ቀጥታ፡

በአንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየቀረበ ያለውን የተሳሳተ መረጃ በአግባቡ መገንዘብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ካናዳውያን ኔትዎርክ ለማህበራዊ ድጋፍ አሳሰበ

አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) በትግራይ እየተከናወነ የሚገኘውን ህግ የማስከበር ተልዕኮ በተመለከተ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየቀረበ ያለውን የተሳሳተ መረጃ በአግባቡ መገንዘብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ካናዳውያን ኔትዎርክ ለማህበራዊ ድጋፍ አሳስቧል፡፡

ማህበሩ የህግ የማስከበር ተልዕኮው በትግራይ ህዝብ ላይ የታወጀ ዘመቻ ሳይሆን አሸባሪውን ቡድን ወደ ህግ ለማቅረብ የሚደረግ ግዳጅ በመሆኑን አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊረዳው ይገባል ብሏል።

የህወሃት ጁንታ ላለፉት 30 ዓመታት አገሪቱን በብቸኝነት በመቆጣጠር በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለመናገር የሚከብድ አሰቃቂ ወንጀል መፈጸሙንም ማህበሩ አስታውቋል፡፡

በዚህ የግፍ ተግባሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በግፍ ያሰቃየ ሲሆን ቶርቸር፣ አስገድዶ መድፈር፣ የአካል ጉዳትና ግድያ ፈጽሞባቸዋል፡፡

በአገሪቱ ተደጋጋሚና የተጭበረበረ ምርጫ በማከናወን 100 በመቶ አሸንፊያለሁ በማለት ፓርላማውን በብቸኝነት በመቆጣጠርና ስልጣኑን በፈላጭ ቆራጭነት በመጠቀም ያሻውን ሲፈጽምም ኖሯል ብሏል፡፡

ከአገሪቱ ካዝና ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመዝረፍ በምዕራቡ ዓለምና በመካከለኛው ምስራቅ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተቀናጣ ህይወት ሲኖሩበት መቆየታቸውንም ማህበሩ አብራርቷል።

እኤአ በ2018 በአገሪቱ የተቀጣጠለውን ሰፊ ተቃውሞ ተከትሎ ከስልጣኑ የተባረረው የህወሃት ጁንታ ወደ ትግራይ በመሸሽና ሴራ በመጠንሰስ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የንፁሃንን ህይወት በግፍ ሲነጥቅ መቆየቱንም እንዲሁ፡፡

ለውጡን ተከትሎ በአገሪቱ የተጀመረው አዲስ አካሄድ በካቢኔ ሹመት ከግማሽ የማያንሱ ሴቶችን ወደ ሚኒስትርነት ያመጣ ሲሆነ ከዚህ በፊት በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉትን ግለሰቦች ጭምር የመንግስት ኃላፊነት ላይ አንዲቀመጡ አድርጓል፡፡

የህወሃት ጁንታ ያለገደብ ይዞት የቆየውን ስልጣን ተገን በማድረግ እንዳሻው ሲፈጽመው የኖረውን ግፍ ለማስቆም በህግ እንዲገዛ ሲጠየቅ አሻፈረኝ ብሏል፡፡

ስልጣኑንም እንዲያስረክብ ሲጠየቅ ፈቃደኛ ባለመሆን በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሞት ሽረት ትግል ማድረጉን አስታውሷል።

ይህን ተከትሎ በመላ አገሪቱ የብሄር ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ የብዙ ንፁሃን ህይወት በግፍ እንዲቀጠፍ ምክንያትም ሆኗል።

በዚህም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ከመሆን ባለፈ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ልታካሄደው የነበረውን ብሄራዊ ምርጫ የኮቪድ ወረርሸኝን ተከትሎ ለማራዘም ስትወስን የህወሃት ጁንታ እምቢተኛ በመሆን ህገ መንግስቱን የጣሰና ህዝብን አደጋ ላይ የጣለ ህገ ወጥ ምርጫ በማከናወነ 98 በመቶ አሸናፊ ነኝ ሲል አውጇል።

በመቀጠልም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊትን በማጥቃት ክህደት ፈፅሟል።

በዚህም በተለይ ከትግራይ ብሄር ተወላጆች ውጭ የሆኑ ወታደሮችን በመለየት በግፍ የገደሏቸው ሲሆን ሴቶችንና ህጻናትን ጭምር የግፍ ፅዋው ተቋዳሽ አድርገዋቸዋል፡፡

ከጥቃቱ በኋላ ጁንታው ቡድን በትግራይ ክልል የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን በማውደም ፀረ ህዝብነቱን ያረጋገጠ ሲሆን ለክልሉ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጠውን የአክሱም አየር ማረፊያም ማውደሙ ተገልጿል።

የአገሪቱ ብሄራዊ ጦር ጥቃቱን ተከትሎ በከፈተው ራስን የመከላከልና ህግ የማስከበር ዘመቻ ጁንታው ተጠናቆ የጁንታውን አባላት ለህግ የማቅረብ ዘመቻው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የወንበዴው ቡድን ያደራጃቸው "ሳምሪ' የተባሉ ወጣቶች በሚሊሻዎችና በፖሊሶች በመደገፍ በማይካድራ 1 ሺህ የሚጠጉ ንፁሃንን  በግፍና በጭካኔ መግደላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሌሎች መሰል አለም አቀፍ ተቋማት አረጋግጠውታል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ከቦታው ድረስ በመሄድ የተፈጸመውን አረመኔአዊ ተግባር ለህዝብ ይፋ አድርጎታል፡፡

በዚህ የህግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይ ህዝብ ለህግ ተገዥ መሆኑን ያረጋገጠበትና በኢትዮጵያዊነቱ ፍፁም የሚኮራና ኢትዮጵያዊነቱን ለድርድር የማያቀረብ መሆኑን አሳይቷል፡፡

በህወሃት ጁንታ ላይ የተደረገው ዘመቻ የሀገር ህልውና እንዲሆም ወንለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ የሀግ ማስከበር ዘመቻ መሆኑም ተብራርቷል።

በአገሪቱ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የሽብር ተግባርና የብሄር ግጭት ለማስቆምም የጁንታው አባላት ተይዘው ለህግ መቅረባቸው አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል ይላል ዘገባው፡፡

ኢትዮጵያዊያንም በአንድ ላይ በመቆም በጁንታው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለሟቋቋምና በትግራይ የደረሰውን የመሰረተ ልማት ውድመት መልሶ ለመገንባት እንዲሁም የተሰደዱትን ለመደገፍ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በጥምረት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

አለም አቀፉ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ የሚከናወነውን ህግ የማስከበር ተልዕኮ በተመለከተ እውነተኛ የሆነውን መረጃ በመከታተል ከተሳሳተና ውሸት ከሆነ ዘገባ ራሱን መጠበቅ አለበት ይላል ማህበሩ፡፡

የህግ ማስከበሩ የተጠናቀቀ በመሆኑ በቀጣይ ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ሂደቱ በሚገባ እንደሚረጋገጥም የኢትዮጵያ ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ባዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም