ቀጥታ፡

እውነት፣ ፍትሃዊነትና ሕዝባዊነት ተልዕኳችንን በብቃት እንድንፈጽም አድርጎናል - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) እውነት፣ ፍትሃዊነትና ሕዝባዊነት ሠራዊቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በአጭር ጊዜ እንዲያጠናቅቅ አስችሎታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ሠራዊቱ ያስመዘገበው ድል የኢትዮጵያ ሕዝብ ኩራት ነውም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መቀሌ ተገኝተው የሕግ ማስከበር ሂደቱን ከመሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት ይዟቸው የተነሳው እውነት፣ ሕዝባዊነትና ፍትሃዊነት የድሉ መሰረት ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጁንታው የዘረፋቸው በርካታ ተተኳሽ የጦር መሳሪያዎች፣ አገር የከዱ የሰለጠኑ ሰዎች ቢኖሩትም በአጭር ጊዜ ተሸንፏል ብለዋል።

ሠራዊቱ በሕዝቡ ላይ አንዳች ጉዳት ሳይደርስ የሕግ ማስከበር ሂደቱን ሲያጠናቅቅ የጁንታው ሃይል ግን በሕዝቡ ላይ ሮኬት በመተኮስ ሕዝባዊ አለመሆኑን በድጋሚ ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከተሞች በሕግ ማስከበር ሂደቱ "ሕዝባችን ላይ አንዳች ጉዳት እንዳይደርስ ያደረግነው ጥረትም ውጤታማ ነበር" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ በሕግ ማስከበር ሂደቱ ያሳየው አንድነትና ወንድማማችነት ዘላቂ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

መንግስት የመከላከያ ሠራዊቱን በበጀት፣ በስልጠናና በዕውቀት ለመደገፍ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

መንግስት በሕግ ማስከበር ሂደቱ የተጎናጸፈውን ድል በልማት ሥራዎችም የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እንደሚደግመውም አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት የሚናገረውን የሚተገብር በመሆኑ 'ትግራይን መልሶ በመገንባት ሕዝባዊነታችንን እናረጋግጣለን' ነው ያሉት፡፡

የሕግ ማስከበር ሂደቱን የመሩ የጦር መኮንኖች ጦሩን የመገንባት ስራ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም