ዳያስፖራው ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ እንዲልክ አሰራሮችና ማበረታቻዎች ሊመቻቹለት ይገባል - በአቡዳቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ እንዲልክ አሰራሮችና ማበረታቻዎች ሊመቻቹለት ይገባል - በአቡዳቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን
አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ገንዘቡን ወደ አገር ቤት በሕጋዊ መንገድ እንዲልክ አሰራሮችን ማስተካከልና ማበረታቻዎች መስጠት እንደሚገባ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አመለከቱ።
በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የተመራ የልዑካን ቡድን ሰሞኑን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበራትና አደረጃጀት መሪዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ በኤጀንሲው እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች፣ ዳያስፖራው በመደራጀት የሚያገኛቸው ጥቅሞች እንዲሁም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የመወያያ ሰነድ ቀርቧል።
በአቡዳቢ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በተደረገው ውይይት ዳያስፖራው ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚልክበትን ሁኔታ በማስቀረት ሕጋዊ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ለሚልኩም ማበረታቻ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ዳያስፖራው አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ተሳትፎ የሚያደርግበት ሁኔታ እንደሚመቻች ጠይቀዋል።
ሕገ-ወጥ የዜጎች ዝውውርን የሚያበረታቱና ከሙስና ጋር የተያያዙ አሰራሮችን ተከታትሎ ማረምና ሕጋዊ አሰራሮችን ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ አንስተዋል።
መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚደግፉና በቀጣይ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አቡዳቢን ጨምሮ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ለወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎች እየሰጡ ላለው ምላሽ አመስግነዋል።
የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ኢትዮጵያዊያኑ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ከመደገፍ ባሻገር በአካባቢያቸው ችግር ላይ ለሚገኙ ዜጎች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ድጋፉ የኢትዮጵያዊያንን የትብብር መንፈስ እንዳሳየም ተናግረዋል።
በዋና ዳይሬክተሯ የተመራው የልዑካን ቡድን በሰሜን ኤምሬቶችና በዱባይ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር መወያየታቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።