ቀጥታ፡

የሻምበል አበበ ቢቂላ 60ኛ ዓመት የሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ድል ተዘከረ

አዲሴ አበባ ታሄሳስ 4/2013 (ኢዜአ) የሻምበል አበበ ቢቂላ 60ኛ ዓመት የሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ድልና ከሜልቦርን እስከ ሪዮ ኦሎምፒክ የአትሌቲክስ ባለድሎችን የሚዘክር መርሃ ግብር ተካሄደ ፡፡

መርሃ ግብሩ "የባዶ እግር ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ  ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዷል ፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የስፖርት ቤተሰቦችና እንግዶች መርሃ ግብሩን ታድመዋል፡፡

በአትሌቲክስ ኢትዮጵያን ወክለው ወርቅ ያመጡ፣ ድል ባይቀናቸውም የተሳተፉ፣ አሰልጣኞች፣ የስፖርት ጋዜጠኞች፣ ሀኪሞችና ወጌሾች የገንዘብና የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የተዘጋጀ ዶክመንተሪ ፊልምም ቀርቧል በመርሃ ግብሩ፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የአበበ ቢቂላ የባዶ እግር ትሩፋቶች ለአሁኖቹ ስፖርተኞች መሰረት መሆናቸውን ተናግራለች፡፡

'እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ድሎች በመዘከር ለአዲስ ድል መስራት ይጠበቀቅብናል' ብላለች።

ለስፖርቱ እድገት ክልሎች ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጎን እንዲቆሙም አሳስባለች፡፡

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው 'ያለፉ የስፖርት ታሪኮቻችን ለቀጣይ ስራችን ትልቅ መደላድል ናቸው፤ ታሪኮቻችንን ለልጆቻችን ማሳወቅ አለብን' ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ የአትሌቲክስ ስፖርት ለኢትዮጵያ ገፅታ ግንባታ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን በማስታወስ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም