ቀጥታ፡

የህወሃት ጁንታን ለማስወገድ የልዩ ዘመቻዎች ኃይልና የሪፐብሊካን ጋርድ ገድል የላቀ ነበር…ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ

ሐዋሳ፤ታህሳስ 4/2013(ኢዜአ) የህወሃት ጁንታን ለማስወገድ በተካሔደው ትግል ውስጥ የልዩ ዘመቻዎች ኃይልና የሪፐብሊካን ጋርድ ገድል የላቀ እንደነበረ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ ገለጹ።

በብላቴ የሚገኘው የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ለ33ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የሪፐብሊካን ጋርድ መሠረታዊ ኮማንዶ አባላትን ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሹማ አብደታ እንዳሉት ጁንታውን ለማስወገድ በተካሄደው ግዳጅ ውስጥ የልዩ ዘመቻዎች ኃይልና የሪፐብሊካን ጋርድ አባላት ገድል የላቀና ወደር የሌለው ነው። 

“የዛሬ ተመራቂዎችም ወደር የሌለውን ጀግና ክፍል በመቀላቀላችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል” ያሉት አዛዡ ተመራቂዎቹ የክፍሉን አንጸባራቂ የጀግንነት ታሪክ ለማስጠበቅ ሊተጉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

“በሀገራችሁ ሰንደቅ ዓላማ ፊት በፈፀማችሁት ቃለ መሀላ መሠረት ከጎሰኝነት፣ከዘረኝነትና ከየትኛውም የፖለቲካ ጥገኝነት ነፃ በመሆን አስፈላጊውን መስዋእትነትን ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለባችሁ” ብለዋል።

“ታላቅ ሀገራዊ ፍቅርና ኢትዮጵያዊ ማንነት ዳግም በተረጋገጠበት ዘመቻ ታልቅ ድል ባስመዘገብንበት ታሪካዊ ወቅት በመመረቃችሁ በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል ።

የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ተዝገራ ከበደ በበኩላቸው የኮማንዶ ተመራቂዎቹ ፈታኝ፣አድካሚ፣ውስብስብ፣እልህ አስጨራሽ የሆነውን ስልጠና በታላቅ ወኔና ጀግንነት ማጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል።

“በስድስት ወር ቆይታቸው በታጠቋቸው የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ማንኛውንም ተንቀሳቃሽና ቋሚ ዒላማዎችን የመደምሰስና የማውደም አቅም እንዲኖራቸው ተደርጓል” ብለዋል።

ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል መሠረታዊ ኮማንዶ አይናለም ብርዬ በሰጠችው አስተያየት በስልጠና ቆይታዋ ግዳጅን በብቃት መወጣት የሚያስችል ችሎታና አቅም መፍጠሯን ተናገራለች።

ሌላኛው ተመራቂ መሰረታዊ ኮማንዶ ጫላ ጋረደው በበኩሉ የሀገሬንና የህዝቤን ሰላም ለማረጋገጥ የሚሰጠኝን ማንኛውንም ግዳጅ በአስተማማኝ ብቃት ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም