ኢትዮጵያ ሁሌም በልባችን ውስጥ የምትኖር ጎረቤታችን ናት - ርብቃ ኒያንግ ጋራንግ

ታህሳስ 4/2013 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ ሁሌም በልባችን ውስጥ የምትኖር ጎረቤታችን ናት" ሲሉ በደቡብ ሱዳን የስርዓተ ጾታ፣ ወጣቶችና ስፖርት ክላስተር ምክትል ፕሬዚዳንት ርብቃ ኒያንግ ጋራንግ ተናገሩ።

የደቡብ ሱዳን ታላቁ ሩጫ በስኬት እንዲከናወን የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የደቡብ ሱዳን ታላቁ ሩጫ "ለሠላም በጎ ምላሽ እንስጥ፤ አገራችንንም መገንባት እንችላለን" በሚል ሃሳብ ትናንት ተካሄዷል።

በውድድሩ አትሌቶችን ጨምሮ ከስምንት ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።

የቀድሞው የደቡብ ሱዳን የነጻነት ተጋይ ጆን ጋራንግ ባለቤትና በደቡብ ሱዳን የስርዓተ ጾታ፣ ወጣቶችና ስፖርት ክላስተር ምክትል ፕሬዚዳንት ርብቃ ኒያንግ ጋራንግ ከሙሉ የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በውድድሩ ተሳትፈዋል።

በደቡብ ሱዳን የታላቁ ሩጫ ማኅበር ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ አቶ አይሸሽም ተካ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ውድድሩ በደቡብ ሱዳን የሠላም ሂደት በጎ ሚና ማበርከትን ዓላማ አድርጎ እ.አ.አ በ2017 ነው የተጀመረው።

የመጀመሪያው ውድድር 'ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ' ጋር በመተባባር እንደተካሄደም አስታውሰዋል።

በወቅቱ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ደቡብ ሱዳናዊያን ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉንም ነው ያወሱት።

በዘንድሮው ውድድር በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ በደቡብ ሱዳን የጾታ፣ ወጣቶችና ስፖርት ክላስተር ምክትል ፕሬዚዳንት ርብቃ ኒያንግ ጋራንግ ለኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ምስጋና አቅርበዋል።

"ኢትዮጵያ በልባችን ውስጥ የምትኖር ጎረቤታችን ናት" ሲሉም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ፍቅር መግለፃቸውን አቶ አይሸሽም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም