ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና አብደላ ሀምዶክ የጋራ ጉዳዮች ውይይት በመግባባት ተጠናቋል

አዲስ አበባ ታህሳስ 4/2013 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና በሱዳኑ አቻቸው አብደላ ሀምዶክ መካከል የተካሄደው ውይይት በበርካታ የጋራ ጉዳዮች መግባባት ላይ ተደርሶ ተጠናቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ዛሬ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ የገቡት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከየልዑካን ቡድኖቻቸው ጋር በመሆን የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።

በአገራቱ መካከል ያለው ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ምቹ መሠረት እንደሆነ  ሁለቱም ወገኖች መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታም የውይይታቸው አካል እንደነበረ ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክም የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ደግሞ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሱዳን እጅግ አስፈላጊ በሆነ ወቅት እንደደረሱላቸው አስታውሰዋል።

 በሁለቱ መሪዎች መካከል የተካሄደው ውይይት በአገራቱ በርካታ የጋራ ጉዳዮች መግባባት ላይ ተደርሶ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ የምታካሂደውን የሕግ ማስከበር ሥራ አስመልክቶ ሱዳን አጋርነቷን መግለጿን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በድረ ገጹ አስነብቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም