ከሀዲውን ጁንታ ለማስወገድ ማንስ ቢሳተፍ?

117

አብዱራህማን ናስር (ኢዜአ)

በትግራይ ክልል በመሸገው የህወሃት ጁንታ ቡድን አመራር ሰጪነት በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ያደረሰው ጥቃት መላው ኢትዮጵያውያንን ያንገበገበ ጉዳይ ነው። የህወሃት ጁንታ ቡድን የጥፋት ተልእኮውን የሚያስፈጽሙለትን አካላት በሰራዊቱ ውስጥ ሰግስጎ በማስገባት ሀገሩንና ህዝቡን ከጠላት ለመከላከል በተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት በማድረስ የሀገር ክህደት ፈጽሟል።

የከሀዲው ጁንታ ቡድን ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አባላት ላይ የፈጸመው ግፍ እንኳን በወገን ላይ ቀርቶ በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ ሊታሰብ የማይችል መሆኑን በስፍራው የነበሩ የሰራዊቱ አባላት ስለድርጊቱ በተለያየ መልኩ ተርከውታል። የሰራዊቱ አባላት እንደሚገልጹት ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት በሰራዊቱ ውስጥ የከሀዲው ጁንታ ቡድን ተላላኪ የሆኑ የሻለቃ አባላት በየቀኑ በሚስጢር ይሰበሰቡ ነበር። ሰራዊቱ ግን የህዝቡን ደህንነት በመጠበቅና በማህበራዊ አገልግሎቶች በመሳተፍ ድጋፍ ሲያደርግ ነበር። ጥቃቱ በተፈጸመበት እለት እንኳ ቀኑን ሙሉ  የአንበጣ መንጋ በማባረር ስራ ላይ አሳልፈዋል። በዚህ ሁኔታ ላይ በነበረ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ነው በሌሊት አብረዋቸው በኖሩ፤ ነገር ግን በከሀዲዎች ከጀርባ የተወጉት።

ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ጥቃት በተፈጸመባቸው ቦታዎች ላይ ተገኝተው ጉዳዩን ካጣሩ በኋላ ስለሁኔታው ሲገልጹ “በእለቱ ድግስ ተደግሶ የመከላከያ ሠራዊት ሃላፊዎች ጥሪ ተደርላቸው ሲሄዱ የሚፈልጓቸውን የክፍለጦር አዛዦችን አፍነዋቸዋል። ማታ 4 ሰዓት ኦፐሬሽኑ ተጀመረ፣ የራዲዮ ኮሙዩኒኬሽን አቋረጡ። ሠራዊቱ እርስ በርስ መገናኘት አይችልም። ብርጌድ አዛዥ ሻለቃውን ማግኘት አይችልም። የክፍለ ጦር አዛዥ ከላይ ያለውን ብርጌዱን ማግኘት አይችልም። ከመከላከያም ክፍለ ጦሩን ማግኘት አይችልም። በውስጥ የራሳቸውን ሰዎች አደራጅተው የእኛን የሬዲዮ መገናኛ እነሱ ከሚፈልጉት አኳያ እንዲሁም ቼይን ኦፍ ኮማንድ በሙሉ ወደ እነርሱ አዞሩት። ምክንያቱም  የመከላከያ መገናኛ ዋና መምሪያ ሃላፊ የጁንታው ቡድን አባል ነው። የሰሜን እዝ ባለባቸው አካባቢዎች በሙሉ የመከላከያን የሬዲዮ ፕሮግራም እነርሱ ብቻ በሚያውቁት መንገድ ፕሮግራም አደረጉ። ይህን ዝግጅት ካደረጉ በኋላ ኦፐሬሽን ጀመሩ።” በማለት ነበር  በወቅቱ ስለተፈጠረው የሀገር ክህደት ተግባር በቁጭት የተናገሩት።

የከሀዲው የጁንታው ቡድን ልዩ ሃይል ሠራዊቱን በሙሉ ከበባ አድርገው "እጃችሁን ስጡ ጠመንጃችሁን አስረክቡና ወደ ፈለጋችሁበት ትሄዳላችሁ፤ እኛ ጠብመንጃ እንጂ እናንተን አንፈልግም የእኛ መንግስት የተመረጠ መንግስት ነው፣ የአዲስ አበባ መንግስት የተመረጠ መንግስት ስላልሆነ ፈርሷል።" በሚል ቅስቀሳና ማስፈራሪያ ነበር ሠራዊቱን መውጋት የጀመሩት።

የጁንታው ቡድን ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ላይ ሰራዊቱ በተኛበት ከውጭም ከውስጥም የጥይት ናዳ አውርዶባቸዋል። ይህም አልበቃ ብሏቸው አስከሬናቸው ላይ ጨፍረዋል፤  አፍነዋቸው የነበሩትን የሰራዊቱ አባላት ዩኒፎርማቸውን አውልቀው መሳሪያዎቻቸውን ቀምተው ራቁታቸውን አባረዋቸዋል። አንድ ሻለቃ ድርጊቱን በተመለከተ የገለጹበትን መንገድ ጄኔራል ባጫ ሲናገሩ "እነዚህ ሰዎች የወጉን ወገኖቻችን ናቸው፣ አብረን ነው የኖርነው ብለን እንደ ሰው ነበር የምናያቸው ነገር ግን የሰው መልክ ያላቸው ከጀሃነም ያመለጡ ሴይጣኖች ስለሆኑ በምድር ላይ ሰው ሆነው ሰው መስለው መኖር የለባቸውም፤ ልንፈቅድላቸውም አይገባም ወደ ጀሃነም ልንመልሳቸው ይገባል" በማለት ነበር የገለጹት።

የጁንታው ታጣቂ ቡድን በሰሜን እዝ ሠራዊት አባላት ላይ ለአእምሮ የሚከብዱ ኢ ሰብዓዊ ድርጊትና ሰቆቃዎችን ፈፅሟል። ቡድኑ በሠራዊቱ ላይ ሲኖትራክ መኪና እንዲሄድባቸው ተደርጎ በአሰቃቂ ሞት ብዙዎችን ለህልፈት ዳርጓል።  በዚህ አጋጣሚ በህይወት የተረፈው የሠራዊቱ አባል ሃምሳ አለቃ ደረጀ አንበሳ እንደሚገልጸው ግራና ቀኙ ገደል በሆነበት ጠባብና ገደላማ ቦታ ላይ የልዩ ሃይል አባላት ዙሪያውን ከብበው ከላይ ዲሽቃ ተጠምዶ በሠራዊቱ አባላት ላይ በሌሊት ሲኖትራክ እንዲነዳባቸው ተደርጓል። “የሰው ልጅ በመሳሪያ ይገደላል እንጂ እንዴት ከባድ መኪና ይነዳበታል፤ እኔም ከጓደኞቼ ጋር ብሞት ይሻለኝ ነበር” በማለት እንባ እየተራጨ የደረሰውን ግፍ ተናግሯል። የጁንታው ቡድን ሽማግሌ መስለው ራሳቸው ትጥቅ አስፈትተዋል፤ አንፈታም ያሉትን አስጨፍጭፈዋል፤ መሳርያ ቆልፈው እራሳቸውን መከላከል እንዳይችሉ አድርገዋል፤ ሊነገር የማይችል ብዙ ግፍ ፈጽመዋል።

ይህ የጁንታው ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ብቻ ሳይሆን የልማት አውታሮችን ከአደጋ ሲጠብቁ በነበሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይም ክህደት ፈጽሟል። ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ በሚጠብቋቸው ተቋማትና መኖሪያ ካምፖች ላይ እንዳሉ ጭካኔ የተሞላበት የግድያና የአፈና ወንጀል ፈጽሞባቸዋል። የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንደሚናገሩት የጁንታው ቡድን የገደላቸውን ማንም ሳይቀብራቸው አሞራ በልቷቸዋል። ተመትተው በየወንዙና በየጫካው የተጣሉም አሉ። ለህክምና መድረስ እየቻሉ ህክምና ተከልክለዋል። ይህ አረመኔያዊ ተግባር የኢትዮጵያ ህዝበ እንዲያውቀው በማለት የደረሰባቸውን ግፍ አስረድተዋል።  

በማይካድራ አካባቢና በሌሎችም ስፍራዎች በንጹኃን ዜጎች ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ግድያ መቼም ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም። የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በስፍራው ተገኝቶ ባካሄደው ጥናት ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት ህግን ለማስከበር ከሃዲውን ቡድን ለህግ ለማቅረብ የጀመረውን ዘመቻ ተከትሎ ማይካድራ በሚኖሩ እና የትግራይ ተወላጅ ባልሆኑ ሰዎች ላይ፣ በተለይም በአማራና ወልቃይት ተወላጆች ላይ ከባድ ስጋት እና ተጽዕኖ ተከስቶ ነበር። ለወቅታዊ የጉልበት ስራ የመጡት ሰራተኞች በከተማው ውስጥ በነፃነት መዘዋወር፣ ወደ ስራ መሄድ እና ወደ መደበኛው መኖሪያ ቦታቸው መመለስ ጭምር ተከለከሉ።

ጥቃቱ ከመከሰቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ ማይካድራ ለመግባት መቃረቡ ሲሰማ፣ ሁሉም ከማይካድራ የሚያስወጡ ኬላዎች በአካባቢው አስተዳደር የሚሊሽያና ፖሊስ ሃይሎች ተዘጉ። ጥቃቱ በጀመረበት ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ 5፡00 ሰዓት አንስቶ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት እና ልዩ ስሙ “ግንብ ሰፈር” በሚባለው መንደር  ፖሊስ የግለሰብ ቤቶችን ፍተሻ አካሂዶ  ስልኮቻቸውን ሰባበሩ። ይህም ጥቃት ሲፈጽሙ ህብረተሰቡ መልዕክት እንዳያስተላልፍና የእርዳታ ጥሪ እንዳያሰማ በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል። ጥቃቱ ከመጀመሩ ጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ በአጥቂው ቡድን አስተባባሪነት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ በተለይ ሴቶች እና ሕፃናት ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ አደረጉ፡፡ በዚያው እለት በግምት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ ሌሊቱን ሙሉ የከተማው ፖሊሶች፣ ሚሊሺያዎች እና ሳምሪ የሚባለው ኢ-መደበኛ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ቡድን በአንድነት በመሆን ወደ ግንብ ሰፈር ተመልሰው በመምጣት ምንም በማያውቁ ንጹሃን ዜጎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል። በወቅቱ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት በትንሹ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ተገልጿል።

ይህን መሰል አረመኔያዊ ተግባር ላይ የተሰማራውን የከሀዲውን ጁንታው ቡድን ለህግ ለማቅረብ መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ መቀሌ ላይ ትእዛዝ የሚሰጠው የቡድኑ አመራር ጉዳዩን ቀጠናዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጓል። ትንኮሳ ልማዱ የሆነው የጁንታው ቡድን ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ወደ አስመራ የሮኬት ጥቃት ሰንዝሯል። በድጋሚ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽሟል። ይህንንም በይፋ ያስታወቀ ሲሆን የሰጠው ምክንያት “የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በትግራይ ላይ በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት በመክፈቱ የተሰነዘረ የአፀፋ ጥቃት ነው” የሚል ነበር። በርግጥ የቡድኑን ድርጊት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አውግዞታል።

ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው የጁንታው ቡድን መሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በክልሉ መገናኛ ብዙሃን “የኤርትራ ወታደሮች ከፌዴራል የፀጥታ ኃይል ጋር ግንባር ፈጥረው እየወጉን ነው። የሀገሪቱ አምባገነን መሪ ከውጭ ሃይል ጋር በመተባበር የትግራይን ህዝብ ለመቀጥቀጥ ዜጋውን ለመጨፍጨፍ ወስኖ እየሰራ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። በተመሳሳይ የሮይተርስ የዜና ወኪልን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን እና የፖለቲካ ተንታኝ ነን የሚሉ አካላት ቡድኑ የፈጸመውን የሀገር ክህደት ወንጀል በማጋለጥ ፋንታ ማረጋገጫ በሌለው ጉዳይ ላይ ጊዜ ሲያጠፉ ታይተዋል። መገናኛ ብዙሃኑም ይሁን የፖለቲካ ተንታኝ ነን ባዮቹ ይህን መሰል መሠረተ ቢስ ወሬ ላይ እንዴት እንደተጠመዱ የሚያጠያይቅ ቢሆንም በውጊያው ላይ ሌሎች አካላት ስለመሳተፋቸው የሚናገሩት የጁንታው መሪዎች የሚሰጧቸውን የፕሮፖጋንዳ መረጃዎች ተቀብለው ነው። ያም ሆነ ይህ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባቱን ምላሽ የሰጠው ወዲያው ነበር። የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ዑስማን ሳልሕ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል "በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም" በማለት አረጋግጠዋል።

የከሃዲው ጁንታ ቡድን የሀገርን ሉኣላዊነት በሚያስከብረው መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ለፈጸመው የሀገር ክህደት ወንጀል ቡድኑን ለማስወገድ የተሳተፈ የውጭ አካል የለም። ይሁን እንጂ ማንኛውም አካል ቢሳተፍ የጁንታው ቡድን ለፈጸመው ጥቃት ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም። ንጹሃን ዜጎችን በጠራራ ፀሐይ ማንነታቸውን መሰረት አድርጎ በጅምላ የሚጨፈጭፍ ወንጀለኛ ቡድንን ለማስወገድ የትኛውም አማራጭ ለመውሰድ የሚያስገድድ ስለመሆኑ ማሰረጃ አያስፈልገውም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ከሰሞኑ በስፍራው ተገኝቶ ምልከታ ካደረገ በኋላ በሰጠው መግለጫ በተለይ በዳንሻ የሰሜን እዝ 5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለጦር መምሪያ ሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በክህደትና ኢሰብአዊ ድርጊት ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸው ላይ ጭምር የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽመው ከአካባቢው እንዲፈናቀሉ መደረጋቸውን አረጋግጧል። በሁመራ ከተማም የጁንታው ቡድን ስድስት ባለሃብቶችን እና በሆስፒታል የነበሩ ታካሚዎችን መግደሉን አክሎ ገልጿል።        

ይህ የህወሃት ጁንታ ቡድን ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያሻውን በፈላጭ ቆራጭነት ሲፈጽም የኖረ ቡድን ነው። የጁንታው ቡድን በትጥቅ ትግል ወደስልጣን በመጣበት ወቅት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ ስለሆነ ከዚህ ባህሪው እስካሁን ድረስ መላቀቅ ተስኖታል። ከሀዲው የጁንታው ቡድን በተለይ ከ1997 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ ወዲህ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ ህጎችን በስራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እንዲሁም ንጹሃን ዜጎችን ለእስር፣ ለሰቆቃና ለእንግልት ዳርጓል። ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሲያወጧቸው በነበሩ ሪፖርቶች በሀገሪቱ ሲፈጸሙ የነበሩ የመብት ጥሰቶች ሲያጋልጡ እንደነበርም ይታወሳል። በ 27 ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙ መከራዎች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች ዋነኛው ተዋናይና ባለቤት የሕወሃት ጁንታ ቡድን ስለመሆኑ በግልጽ የተነገረ ሲሆን በተለይ ዋና ዋና የሚባሉ የአገሪቱን ተቋማት እንደመከላከያ፣ ደህንነት፣ የኢኮኖሚ ተቋማት በሙሉ ተቆጣጥሮ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ ያሻውን ሲያደርግ የነበረ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ የቡድኑን ገመና የገለጠ ስለነበር ከሀዲው ቡድን አመራሮቹን ሰብስቦ ወደ መቀሌ በመመሸግ ሀገሪቱን ሲያተራምስ ቆይቷል። በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ህብረተሰቡ እርስ በርስ እንዲጋጭ አድርጓል። በዚህም የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ጁንታው በህዝቡ መካከል ጥላቻን በመዝራቱ “እኛና እነርሱ” እንዲባባሉ አድርጓል። ሰው ወዳድ የሆነው የትግራይን ህዝብ “ጠላት አለብህ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊወጋህ ነው” በሚል ተረት ከማህበራዊ መስተጋብር ውጪ ሊያደርጉት ሞክረዋል።  ከሀዲው የጁንታው ቡድን በዚህ ሁኔታ ቢቀጥል ኖሮ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ ይወድቅ እንደነበር ባለፉት ሁለት ዓመታት ካጋጠሙ ሀገራዊ ሁኔታዎች መገንዘብ ይቻላል።

ይህ መሰሪ ቡድን ክፋቱ ወደር የማይገኝለት ከመሆኑ የተነሳ ዓለም የክፋት ጥግ ከወዴት ነው ብሎ ቢጠይቅ ሊማርበት የሚችል ነው። ቡድኑ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የከፈተው ጥቃት መጥፊያውን አፋጥኖታል። መከላከያ ሠራዊቱ ግን  በአኩሪ ድል ፈተናውን ከመሻገሩም በላይ ወደ ፊትም ትልልቅ አገራዊ ፈተናዎች ቢከሰቱ ሀገሩን እንደማያስደፍር አረጋግጧል። እናም ይህን መሰል ከሀዲ ለማስወገድ ሌላ አካል አልተሳተፈም እንጂ ማንስ ቢሳተፍ ምን ክፋት አለው?

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም