ከአገራዊ ለውጡ በፊት ለልማት የተመደበ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ባለመዋሉ አገሪቷን ለተጨማሪ ወጪ ዳርጓል - አቶ አቤ ሳኖ - ኢዜአ አማርኛ
ከአገራዊ ለውጡ በፊት ለልማት የተመደበ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ባለመዋሉ አገሪቷን ለተጨማሪ ወጪ ዳርጓል - አቶ አቤ ሳኖ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3 /2013(ኢዜአ) ከአገራዊ ለውጡ በፊት ለልማት የተመደበ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ባለመዋሉ አገሪቷን ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ተናገሩ፡፡
የኢትጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ ሙስና ቀን አክብረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ “ቀደም ሲል ለልማት የተመደበ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ባለመዋሉ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ውስጥ እንዳይጠናቀቁ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።
ይህም አገሪቷን ለተጨማሪ ወጭ የዳረጋት እንደሆነ ገልጸዋል።
ባልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ምክንያት አገሪቷ የተበደረችውን ገንዘብ በመክፈል ሂደት ጫና ማሳደሩንም የባንኩ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል።
"ገንዘቡ ለታለመለት ዓላማ ውሎ ቢሆን ኖሮ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥር ነበር" ያሉት የባንኩ ፕሬዚዳንት፤ "ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለአገራችን ሰላምና ልማት የማይፈለጉ ኃይሎች በየጊዜው የመዘበሩትን ሀብት ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ አውለውታል" ብለዋል፡፡
የባንኩ ፍላጎት ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት ሲሰጡ ማየት መሆኑን ጠቁመው፤ "ይስተዋሉ የነበሩ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በማረም የአገሪቱን የብልፅግና ጉዞ እንፋጥናልን" ብለዋል፡፡
ለዚህም በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት 47 የሥራ ክፍሎች እና በ71 ቅርጫፎቹ ላይ ከስነ ምግባር አንፃር የዳሰሳ ጥናት ተካሄዶ ለ575 ሠራተኞች የሙያ ስነ ምግባር ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን 3 ሺህ 211 የባንኩ ሠራተኞች ሀብትና ንብረታቸውን ማስመዝገባቸውን አስታውስው፤ ከእነዚህ መካከል ለ1 ሺህ 375 ሠራተኞች የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል ባንኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑም ተናግረው፤ ባንኩ የፀረ ሙስና ቀንን ለማክበር ባዘጋጀው መድረክ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በዚሁ በዓል ላይ በመስሪያ ቤቱ የሙያ ስነ ምግባራቸውን አክብረው በመስራት የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ሠራተኞች የእውቅና እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።