በይርጋ ጨፌና ከፍሰሃ ገነት እስከ ጭኮ ያሉ የመንገድ ግንባታዎች ስምንት አመት ቢሞላቸውም ሊጠናቀቁ አልቻሉም - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በይርጋ ጨፌና ከፍሰሃ ገነት እስከ ጭኮ ያሉ የመንገድ ግንባታዎች ስምንት አመት ቢሞላቸውም ሊጠናቀቁ አልቻሉም - ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3 /2013 (ኢዜአ) በይርጋ ጨፌ እንዲሁም ከፍሰሃ ገነት እስከ ጭኮ ያሉ የመንገድ ግንባታዎች ስምንት ዓመት ሙሉ በመጓተታቸው ችግርና እንግልት እየገጠማቸው መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበኩሉ ችግሩን በመፍታት ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።
የተለያዩ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ የጥራት መጓደልና በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ያልተጠናቀቁ መንገዶች ጉዳይ የበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄ ሆኗል።
የይርጋ ጨፌ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከጥሬ-እቃ ብክነት እስከ ዲዛይን ችግር እንዳለበትና ረዥም ጊዜ የወሰደ ስለመሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
መንገዱ ከተጀመረ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሮ እስካሁን አለመጠናቀቁን ገልጸዋል።
የመንገድ ፕሮጀክት አፈጻጸም ሂደቱ ላይ የሚስተዋሉ የጥራት ጉድለቶችና አዝጋሚ መሆን እንዲቀረፍ የሚመለከተው የመንግሥት አካል የቅርብ ክትትል እንዲያደረግም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
የህብረተሰቡን ጥያቄ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
“በዚህም ይርጋ ጨፌን ጨምሮ እስከ ጭኮ ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋለውን የጥራት መጓደልና መዘግየት ችግር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እልባት ያገኛል” ብለዋል።