የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት አንዲሳካ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት አንዲሳካ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ ሃምሌ 12/2010 ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተደረገው አቀባበል የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ወዳድነቱን ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ህዝብ ጭምር ያሳየበት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ። ሚኒስቴሩ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅና እና ምስጋና ፕሮግራም አዘጋጅቷል። በብሄራዊ ቤተ መንግስት በተካሄደው በዚህ ፕራግራም ላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብን የሚወክሉ ተወካዮችና የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ተካሂዷል። ዶክተር ወርቅነህ ገበየው በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት "ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ላደረጉት ጉብኝት ውጤታማነት መላው የኢትዮጵያን ህዝብ እናመሰግናለን" ብለዋል። ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተደረገው አቀባበል የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ወዳድነቱን ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ህዝብ ጭምር ያሳየንበት ክስተት መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል። በዝግጅቱ ላይ የመንግስትና የግል ተቋማት ተወካዮች፣ የፀጥታ አካላት፣ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች እና ሌሎች ግለሰቦች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሐምሌ 7 እስከ 9 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።