ቀጥታ፡

የካ ክፍለ ከተማ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ 159 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አሰባሰበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3/2013 (ኢዜአ) የካ ክፍለ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባካሄደው የድጋፍ ንቅናቄ 159 ሚሊዮን ብር ማሰባሰቡን ገለጸ።

ክፍለ ከተማው የሕዳሴውን ግድብ ዋንጫ ዛሬ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስረክቧል። 

በአዲስ አበባ ደረጃ ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ ለማሰባሰብ የግድቡ ዋንጫ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተዘዋወረ ይገኛል።

ዋንጫው በየካ ክፍለ ከተማ በነበረው የአንድ ወር ቆይታ "አንድነታችንን በማጠናከር አሻራችንን እናድሳለን" በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ሽያጭ፣ በስጦታና በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ድጋፍ ተሰባስቧል።

የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ የግድቡ ዋንጫ በክፍለ ከተማው ከህዳር 6 እስከ ታህሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም መቆየቱን አስታውሰዋል ።

በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከልዩ ልዩ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፓኬጆችና የቦንድ ግዥ 70 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበረም ነው የገለጹት።  

በዋንጫው የቆይታ ጊዜም ከስጦታ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣ ከቦንድ ግዥ ደግሞ ከ154 ሚሊዮን 895 ሺህ ብር በድምሩ 159 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ከዕቅድ በላይ መሳካቱን ተናግረዋል።   

የክፍለ ከተማው ነዋሪ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ "ግድቡ ከውስጥም ከውጭም ያጋጠመንን ፈተና ተቋቁመን በውስጥ አቅማችን ብቻ ተዓምር መፍጠር እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ዳግማዊ አድዋችን ነው" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የከፍታ ወቅት ላይ ስለመሆኗ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።   

ኢትዮጵያዊያን ሳይለያዩ በገንዘብ፣ በእወቅትና በጉልበት ለግድቡ ያደረጉት ድጋፍ ግድቡ አሁን ላለበት ወሳኝ ምዕራፍ እንዲደርስ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ግድቡ ወደ ብልጽግና ለመሸጋገርና ሁሌም ህዝብ እንደሚያሸንፍ አንድ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።   

"አገሪቷን ወደ ብልጽግና የማሸጋገሩ ሂደት ጥንካሬን ይጠይቃል" ያሉት ኃላፊው፣ ለዚህ ደግሞ አንድነትን ማጠናከርና አሻራ ማኖር ከሁሉም እንደሚጠበቅ ነው ያመለከቱት።

የአዲስ አበባ ከተማ የታላቁ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ በተያዘው ዓመት በከተማ ደረጃ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የሕዳሴውን ዋንጫ ዛሬ የተረከበው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚቀጥሉት 20 ቀናት ውስጥ 212 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ማቀዱ በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ ተገልጿል።

በየካ ክፍለ ከተማ ድጋፍ የማሰባሰብ ሂደት ላይ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን፣ የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ ወረዳዎችም የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል።

በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም