ቀጥታ፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረስላሴ ወግደረስ በ75 ዓመታቸው አረፉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3 /2013(ኢዜአ) የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረስላሴ ወግደረስ ባጋጠማቸው የልብ ህምም ምክንያት በየረር ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ማለዳ በ75 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ከጳጉሜን 5 ቀን 1979 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 29 ቀን 1982 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ኢዜአ ከቅርብ ወዳጆቻቸው ካገኘው መረጃ ለመረዳት እንደተቻለው፤ የቀብር ስነ-ስርዓታችውን የሚያስተባብር ኮሚቴ ተቋቁሞ ቀብራቸው የሚፈጸምበት ቀን ወደፊት ይገለጻል።

ፍቅረስላሴ ወግደረስ የተወለዱት ሐምሌ 7 ቀን 1937 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተለምዶ ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው።

በኢትዮጵያ አየር ኃይል ማሰልጠኛ ወጣት ካዴት ሆነው በመግባት በ1955 ዓ.ም የተመረቁ ሲሆን በአሜሪካ አገርም ስልጠና ወስደዋል።

የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ አየር ሃይልን ወክለው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባል እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተለያዩ የስልጣን እርከኖች አገራቸወን ያገለገሉት ፍቅረስላሴ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) አደራጅ ኮሚቴና የደርግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ።

"እኛና አብዮቱ እና እኔና አብዮቱ” በሚል ርዕስ ሁለት መጽሐፍት ጽፈው ለአንባብያን አድርሰዋል።

ፍቅረስላሴ ወግደረስ ጨምሮ 42 የደርግ አመራሮች በ1989 ዓ.ም በግድያ፣ በዘር ማጥፋትና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን በ2000 ዓ.ም የፍርድ ሂደቱ ሲጠናቀቅ በተከሰሱበት ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ነበር።

በ2003 ዓ.ም የፍቅረስላሴንና ሌሎች 23 የደርግ አመራሮች የሞት ቅጣት ተነስቶ በ2004 ዓ.ም ከእስር እንዲፈቱ መደረጉ አይዘነጋም።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ በተለይም የኢትዮጵያ ታሪክ ለትውልድ ተሰንዶ እንዲቀመጥ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ እንደሚታወቁ ይነገራል።

ፍቅረስላሴ ወግደረስ የሁለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም