በዱባይና በሰሜን ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለሰብአዊ ድጋፍ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
በዱባይና በሰሜን ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለሰብአዊ ድጋፍ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ገቡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3/2013 (ኢዜአ) በዱባይና በሰሜን ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሰብአዊ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ።
በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የተመራ የልዑካን ቡድን በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበራትና አደረጃጀት መሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ውይይት አድርጓል።
ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎች ዳያስፖራው እየሰጠ ላለው ምላሽና ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በኤጀንሲው እየተከናወኑ ያሉ ዋና ዋና ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች፣ የዳያስፖራው መደራጀት ያለው አንድምታ እንዲሁም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰነድ ለውይይት ቀርቧል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግስት ተገዶ ወደ ህግ ማስከበር ስራ እንዲገባ መደረጉና የተወሰደው እርምጃ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
ዳያስፖራው ባካበተው ዕውቀትና ልምድ አገሩን ለማገዝ ዝግጁነት እንዳለውና የተለያዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን በጋራ ለማሰባሰብ እየተሰራ መሆኑም ነው የተጠቆመው።
የዳያስፖራው አባላት ከልዩነት ይልቅ አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው መግለጹንም ተናግረዋል።
ጊዜው የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚጠይቅ በመሆኑ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በተለይ በሀገር ጉዳይ ከልዩነት ይልቅ የጋራ መግባባቶችን መፍጠር ይጠበቅበታል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።
ዜጎች ወደ ዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች በህጋዊ መንገድ መጥተው መስራት እንዲችሉ የተጀመሩ አሰራሮች በፍጥነት ወደ ተግባር ባለመግባታቸው የተፈጠረውን ህጋዊ ያልሆነ አካሄድ ማስተካከል እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ከዚህ በፊት ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በዱባይና በሰሜን ኤምሬቶች የሚኖሩ ዜጎች በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 50 ሺህ ድርሃም (520 ሺህ የሚጠጋ የኢትዮጵያ ብር) ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በተጨማሪም ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።
የልዑካን ቡድኑ ወደ አቡዳቢ በማቅናት በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በከተማው ከሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር እንደሚወያይ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ የተመራ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ፣ ጂዛን፣ ሪያድ እና ደማም በዜጎች መብት እና ደህንነት ማስጠበቅ እንዲሁም በዳያስፖራውና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ጋር ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው።