የኤቲ ኤም ማሽኖች አሁንም የተስተካከለ አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም-ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኤቲ ኤም ማሽኖች አሁንም የተስተካከለ አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም-ተጠቃሚዎች
አዲስ አበባ ሀምሌ12/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኤቲኤም ማሽኖች አለመስተካከል እንቅስቃሴያቸው ላይ አሁንም ጫና ማሳደሩን ተጠቃሚዎች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ችግሩ የተፈጠረው ለተጠቃሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ያለውን አዲስ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረጉ አንዳንድ የቴክኒክ ክፍተቶች መፈጠሩን በመግለጽ ችግሩን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጿል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የባንኩ ኤ ቲ ኤም ማሽን ተጠቃሚዎች እንደገለጹት፤ ማሽኑ ገንዘብ ማውጣት በሚፈልጉበት ወቅት በአግባቡ አገልግሎቱን መስጠት ባለመቻሉ ሳቢያ በስራቸው ላይ መስተጓጎል መፈጠሩን ተናግረዋል። የባንኩን የኤ ቲ ኤም ማሽኖች በተለይም ከስራ ሰዓት ውጪ ባሉት ጊዜያት ለመጠቀም አዳጋች መሆኑን የገለፁት አስተያየት ሰጪዎቹ ይህም ገንዘባቸውን በፈለጉበት ወቅት ማንቀሳቀስ ባለመቻላቸው በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑን ነው ያብራሩት። የባንኩ የኤ ቲ ኤም ማሽኖች ላይ አዲስ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ መደረጉ ችግር ማስከተሉን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ ችግሩ በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታ ተቋሙ ቢገልጽም እስካሁን ድረስ ግን በማሽኑ መገልገል እንዳልቻሉ ነው የገለጹት። ወጣት ፍቅሩ ቶልቻ "የኤቲኤም ማሽኖች አገልግሎት በፊት ጥሩ ነበር። አሁን ግን አገልግሎት አሰጣጡ የዘገየ ነው። ሰዓቱን ጠብቆ የሚወጣ ሰራተኛ በኤ ቲ ኤም ካርዱ መጠቀም አልቻለም። ካሩዱም ለምን አይቀርም የሚባል ደረጃ ላይ ነው እየተደረሰ ያለው።ተስተካክሏል ይላሉ ግን ማስተካከያ የተደረገለት ነገር ብዙም አጥጋቢ አይደለም። አሁን የመጣው አዲስ አሰራር ከህብረተሰቡ ጋር የተጣጣመና ህዝቡ የገባው አይመስለኝም እና ለህብረተሰቡ እንዲገባውና እንዲረዳው ማድረግ ቢቻል ጥሩ ነው “ ብሏል፡፡ ወጣት የሚ ደምሴ በበኩሉ “በፊት ጥሩ አገልግሎት እናገኝ ነበር፣እኔ የግል ኮሌጅ ተማሪ ነኝ ክፍያ ልከፍል ፈልጌ አገልግሎት ማግኘት አልቻልኩም እየተቸገርኩኝ ነው። ብር ፍለጋ እየዞርኩ ነው ግዜዬን እየተሻማብኝ ነው “ የባንኩ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ በበኩላቸው የባንኩ ኤ ቲ ኤም ማሽኖች ተጠቃሚዎች ላቀረቡት ቅሬታ እንዲህ ሲሉ ምላሽ ሰተዋል። " አዲሱን ስዊች መጠቀም የፈልግነው የኤ ቲ ኤም ደንበኞቻችን ቁጥር እያደገ በመምጣቱ ያንን ማስተናገድ የሚችል ስዊች መቀየር ስላለብንና ያንም ማድረጉ የተሻለ አገልግሎት ለመሰጠት ነው፤ በዚህም ምክንያት የአገልግሎት መስተጓጎል ተፈጥሯል፤ ያንን ችግር ለመፍታት ባንኩ ጥረት እያደረገ ነው ፤ የምንችለውን በአዲሱ ስዊች አየቀየርን ነው ጎን ለጎን ደግሞ አሮጌውም ስዊች እዲሰራ እያደረግን ነው። ግን አልፎ አልፎ አዲስ ቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ አዲሱ ቴክኖሎጂ ላይ ትንሽም ስህተት ቢኖር አገልግሎት መስጠት ያቋርጣል፤ አዲሱ ደረሰኝ ከሌለው ላይሰራ ይችላል በትንሽም ስህተት አልፎ አልፎ አገልግሎቱ ማቋረጥ ያጋጥማል፤ ለዚህም ደንበኞቻችን በቅርብ ቀናት ውስጥ የተሻለ አገልግሎት ያገኛሉ የሚል እምነት አለኝ።”ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ቴክኖሎጂው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ተጠቃሚዎች አሰራሩን ባለመረዳት በሚፈጥሩት ስህተት አልፎ አልፎ አገልግሎቱ ሊቋረጥ እንደሚችልም ጭምር ነው ያብራሩት። አዲሱ አሰራር ለደንበኞች ምቹ እንዲሆን ታስቦ የተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የባንኩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አዲሱን አሰራር ለተጠቃሚው ግልጽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።