ጁንታው ለአመታት የተዘጋጀበትን ጦርነት እኛ በሁለት ሳምንት አጠናቀነዋል፤ አሁን ወንጀለኞችን በማደን ላይ ነን-- ጀነራል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2013 (ኢዜአ) ጁንታው ለአመታት የተዘጋጀበትን ጦርነት እኛ በሁለት ሳምንት በማጠናቀቃችን አሁን ወንጀለኞችን በማደን ላይ ነን ሲሉ የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

ጀነራል ብርሃኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመከላከያ ሰራዊት ባደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሰራዊቱን በመደገፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረገው ድጋፍና  እገዛም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ጀነራሉ በንግግራቸው የሰሜን እዝ ሰራዊት ለትግራይ ህዝብ ያልከፈለው ዋጋ የለም ብለዋል።

ሰራዊቱ ትግራይ ላይ በመቀመጡ ብቻ በሚያወጣቸው ወጭዎች በየዓመቱ አራት ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

ይህን ሁሉ ነገር ሲያደርግ በነበረ እዝ ላይ ጁንታው የፈፀመው ጥቃት የአውሬነት ድርጊት ነው ብለዋል ጀነራል ብርሃኑ።

ጁንታው ያደረሰው ጥቃት አንድ ሆኖ ብቻውን ሲሰራ የነበረውን ወታደር እንደ አስር ግለሰብ እንዲሰራ አድርጎታል ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህ ጥቃት የተፈጠረው እልህ፣ ወኔና ቁጭት በሰራዊቱ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የጀግንነት ስሜት እንደፈጠረም ጠቁመዋል።

ጁንታው ለሁለት አመት ሲያደርግ የነበረውን የውጊያ ዝግጅትም እኛ በሁለት ሳምንት ውስጥ በድል አድራጊነት አጠናቀነዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ሰራዊቱን ለማጠናከር በአጭር ጊዜ ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍ ጄኔራል ብርሃኑ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም