ኢትዮጵያ በሱዳን ብሉናይል ግዛት በኩል በምትዋሰንበት አካባቢ ሠላምን የሚያውክ ተግባር እንደማይኖር የግዛቱ አስተዳዳሪ አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሱዳን ብሉናይል ግዛት በኩል በምትዋሰንበት አካባቢ ሠላምን የሚያውክ ተግባር እንደማይኖር የግዛቱ አስተዳዳሪ አስታወቁ
አሶሳ፣ ታህሳስ 02 /2013( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በሱዳን ብሉናይል ግዛት በኩል በምትዋሰንበት አካባቢ ሠላም የሚያውኩ የትኛውም ተግባር እንደማይኖር የግዛቷ አስተዳዳሪ አስታወቁ፡፡
በኢትዮጵያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት የጋራ የሠላም እና የጸጥታ መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምራል፡፡
በሱዳን የብሉናይል ግዛት አስተዳዳሪ ሚስተር አብዱራህማን ኑረዳኢ በወቅቱ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት በምስራቅ አፍሪካ ሠላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
አሁን ያለው የሱዳን መረጋጋት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ያመለከቱት አስተዳዳሪው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መረጋጋት ለሱዳን ሠላም ወሳኝ እንደሆነ የተናገሩት አስተዳዳሪው በኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ መኖሩን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሱዳን ብሉናይል ግዛት በኩል በምትዋሰንበት አካባቢ ሠላም የሚያውክ የትኛውም ተግባር እንዳይኖር የግዛቱ ህዝብ እና መንግስት በትኩረት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎችም ጉዳዮች እንደሚመሳሰሉ የገለጹት ሚስተር አብዱራህማን የአካባቢውን ሠላም ለማስቀጠልና ለህዝቦች መቀራረብ በበለጠ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ህዝቦቻችንን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅም ወቅቱ የሚጠይቀን ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ብልጽግና ለማረጋገጥ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በህዝቦች የጋራ ርብርብ እየተገነባ የሚገኘውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በምሳሌነት የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮጀክቱ ሱዳናዊያንንም ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።
የሱዳን ሠላም የኢትዮጵያ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ አሻድሊ ክልሎቹ ባለፉት ዓመታት በሠላም እና ጸጥታ መስክ ባከናወኗቸው ተግባራት የአካባቢውን ህዝቦች አንድነት የሚያጠናክር ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ይኸው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በጋራ መድረኩ የሁለቱ ሃገራት ክልሎችን የወከሉ ከ50 የሚበልጡ ልኡካን እየተሳተፉ ነው፡፡
መድረኩ እስከ ነገ እንደሚቀጥል፣ ክልሎቹ አዲስ የጋራ የሠላም እና ጸጥታ ስምምነት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ሲል ሪፖርተራቸን ከአሶሳ ዘግቧል፡፡