ቀጥታ፡

ሀገራችንን ወደ ዕድገት ማማ በማስፈንጠር አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን የሚያስችላት የዐሥር ዓመት ብሔራዊ ዕቅድ ጸድቋል... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 2/2013(ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ፣ ሀገሪቱን ወደ ዕድገት ማማ በማስፈንጠር አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን የሚያስችላት የኢትዮጵያ የዐሥር ዓመት ብሔራዊ ዕቅድ ማጽደቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው እንዳሰፈሩት ዕቅዱ በተለይም በሰላም ግንባታ እና ተቋማዊ ሕዳሴ ላይ የሚያተኩሩ ዐሥር ምሦሦዎች አሉት።

በተጨማሪም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኅትመት እና የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን መተዳደሪያ ሆኖ የሚያገለግለውን እና ለማኅበራዊ ሚዲያ የሕግ ማሕቀፍ ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚተገበረውን ረቂቅ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አዋጅ ማጽደቁንም ገልጸዋል።

"የዘርፉን ግዴታዎች እና ኃላፊነቶች የሚተነትነው ዐዋጅ፣ የመረጃ እና የፕሬስ ነጻነት ተግባራዊነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚደግፍ ነው" ሲሉም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም