የሕወሃት ቡድን እኔን አፍኖ ለመያዝ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ አድርጓል... ፖለቲከኛና ፀሃፊው አንዳርጋቸው ጽጌ - ኢዜአ አማርኛ
የሕወሃት ቡድን እኔን አፍኖ ለመያዝ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ አድርጓል... ፖለቲከኛና ፀሃፊው አንዳርጋቸው ጽጌ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2013(ኢዜአ) የሕወሃት ቡድን እኔን አፍኖ ለመያዝ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ አድርጓል ሲሉ ፖለቲከኛና ፀሃፊው አንዳርጋቸው ጽጌ ተናገሩ።
ከዚህ ወጭ የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ ጌታቸው አሰፋ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላሩን በአሜሪካን አገር በራሱ የባንክ አካውንት ማስቀመጡንም መረጃው አለኝ ብለዋል።
ፖለቲከኛው አንዳርጋቸው ጽጌ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ፖለቲከኛው የህወሃት ቡድን አገር እየመራ በነበረበት ወቅት " አሸባሪ" ተብለው በህወሃት ቡድን የመን ሰንአ ኤርፖርት ላይ ታፍነው በግፍና እንግልት ወደ አገር ቤት መምጣታቸውን ያስታውሳሉ።
ከዙህ በኋላ በእስራት በቆዩባቸው ዓመታትም በርካታ እንግልትና ስቃይ ደርሶባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህ አጋጣሚ ታስረው በነበረበት ወቅት ራሳቸውን "የኢትዮጵያ መንግስት እስረኛ ሳይሆን የወያኔ እስረኛ" መሆናቸውን ይረዱ እንደነበርም ገልጸዋል።
ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት እስርቤቶችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፍትህ ስርዓቱ ላይ ፈላጭ ቆራጭና አፋኝ ስለነበር እንደፈለገ ወንጀል ሲፈጽም መቆየቱንም ያስታውሳሉ።
የህወሃት ቡደን የአገሪቷን ተቋማት በሙሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በራሱ ሰዎች ተቆጣጥሮ ግፍና በደል እንዲሁም ዘረፋ ሲያካሂድም ኖሯል ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ ቡድኑ ብሄራዊ ጥቅምንና ደህንነትን አሳልፎ መስጠት መገለጫው ነው ብለዋል።
የህወሃት ቡድን አገር እንዲበተን በመጣር በዘርና ማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በማራመድ ሀገራዊ አንድነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያላደረገው ነገር የለም በማለትም ገልጸዋል።
ትልልቅ ፋብሪካዎችና የፋይናንስ ተቋማት ጭምር በብሄር እና በክልል ታጥረው እንዲቀመጡ በማድረግ በኢትዮጵያዊያን መካከል መተሳሰር ሳይሆን መበታተን ለመፍጠር ጥሯል ብለዋል።
ቡድኑ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የዜጎችን ጥፍር ሲነቅል፣ ሲገድል ዜጎች እንዲሰደዱ ሲያደርግ የቆየ የጨካኞች ስብስብ እንደነበርም አስታውሰዋል።
"የሕወሃት ቡድን እኔን ከየመን ሰንአ ኤርፖርት አፍኖ ለመያዝ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ አድርጓል" ሲሉም አስታውሰዋል።
ከዚህም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላሩን በወቅቱ ለነበሩት የየመን ሹማምንት ቡድኑ ገቢ ማድረጉን በመግለጽ፤ ቀሪው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ ጌታቸው አሰፋ በአሜሪካን ሀገር በራሱ የባንክ አካውንት ማስቀመጡን መረጃው አለኝ ብለዋል።
ዘራፊ የህወሐት ቡድን ከኢትዮጵያ ህዝብ የዘረፈውን ሃብትና ንብረት የዓለም አቀፍ ሚዲያ ትኩረት እንዳይሆን እና የውጭ መንግስት ተጠያቂ እንዳያደርጉት ለአንዳንዶች የዘረፈውን ሃብት ያጋራ እንደነበር አንስተዋል።
ለአንዳንድ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና አማላጆች ከአገር ላይ ከመዘበረው ሀብት ላይ በማካፈል የህዝብ ንብረትና ሃብት ሲበትን ኖሯልም ነው ያሉት አቶ አንዳርጋቸው።
አሁን ላይ ለህዝቡ ሲኖር በነበረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ባደረሰው ጥቃትና የዜጎች ጭፍጨፋ የቡድኑ የመጥፊያው ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት።
በመጨረሻም "የህወሃት ቡድን ለህዝብ ሳይሆን ለራሱ፣ ለሀገር አንድነት ሳይሆን ለመከፋፈል፣ ለእውነት ሳይሆን ለሌብነት ሲሰራ ኖሮ ወደ መቃብር ወርዷል" ብለዋል አቶ አንዳርጋቸው።