ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያለ ምንም እንቅፋት የሠላም ማስከበር ተልዕኮዋን እየፈጸመች ነው - ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዋን እንደወትሮው ያለምንም እንቅፋት በመፈፀም ላይ እንደምትገኝ የመከላከያ ሠላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ገለፁ።

ሌተናል ጄኔራል ደስታ አንዳንድ የጁንታው ተላላኪዎች የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ተከፋፍሏል በማለት የሚነዙት አሉባልታ መሰረተ ቢስ መሆኑንም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በ'አሚሶም' ጥላ ስር በሶማሊያ፣ በሱዳን ዳርፉር፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ደግሞ የአቢዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ሃይል 'ዩኒስፋ' ጥላ ስር ሠላም እያስከበረች ነው።

በደቡብ ሱዳን ጁባ በጥቅሉ 11 ሺህ ገደማ ወታደሮችን በማሰለፍ በቀጣናው የሠላም ማስከበር ስራዋን እያከናወነችም ነው።

ኢዜአ የኢትዮጵያ ሠላም አስካባሪ ኃይል ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት ከሠላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊው ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ሌተናል ጄኔራሉ ባለፈው ወር የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ኢ-ሠብዓዊ ተግባርና መንግስት የወስደውን የሕልውናና የሕግ ማስከበር ዘመቻ በማስታወስ ወቅታዊ ሁኔታውን አብራርተዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት በአገር ውስጥ የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጀመሩን ተከትሎ በውጭ አገር ላሉት ሠላም አስከባሪዎች ስለተፈጠረው ሁኔታ ገለጻ መደረጉንም ገልጸዋል።

በዚህም በሁሉም ቀጣና የሠላም ማስከበር ተግባር ላይ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት ድርጊቱን ማውገዛቸውንና የተወሰደውንም እርምጃ ማድነቃቸውን ተናግረዋል።

ሠራዊቱ ያለምንም እንቅፋት የተለመደ የሠላም ማስከበር ተልዕኮውን መቀጠሉንም ገልጸዋል።

ሌተናል ጄኔራል ደስታ የጁንታው ተላላኪዎች በሠላም አስካባሪው የኢትዮጵያ ሠራዊት መካከል መከፋፈል አለ በሚል የሚነዙት አሉባልታ መሰረተ ቢስ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሰሞኑንም በተለያዩ የተልዕኮ ቀጣናዎች የሠላም አስከባሪ ወታደሮች ልውውጥ በተለመደው መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት በቂ አቅም የፈጠረ በመሆኑ በአገር ውስጥ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምክንያት በሠላም ማስከበር ላይ የሚገኝ ሠራዊት ወደ አገር አለመጠራቱንም አክለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የኢትዮጵያ ምልክት የሆነው የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ወደፊትም በተሻለ መልኩ ይቀጥላል።

ሌተናል ጄኔራል ደስታ የአገር መከላከያ ሠራዊቱ ከራሱ ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ ቅድሚያ ሰጥቶ መስዋዕት የሚሆን "የኢትዮጵያ ሠራዊት" እንጂ የፓርቲ ወይንም የግለሰብ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

በሁሉም ግዳጅ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት እንደወትሮው ሁሉ ተልዕኮውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባሰማራቻቸው የሠላም አስከባሪ አባላት ሙገሳና ክብርን አትርፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም