የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ትጥቁን በማምረት ራሱን እንዲችል መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ትጥቁን በማምረት ራሱን እንዲችል መስራት ይገባል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቴክኖሎጂ ጥገኝነት ወጥቶ ወታደራዊ ትጥቁን አምርቶ ራሱን እንዲችል መስራት እንደሚገባ በኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የታሪክ ተመራማሪ አቶ ገስጥ ተጫኔ ተናገሩ።
የታሪክ ተመራማሪው ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የተደራጀውን የመከላከያ ሠራዊት መዋቅርና አሰላለፍ ለውጥ በማድነቅ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
በጦር ሠራዊት ታሪክ ላይ በርካታ መጽሐፍት ለሕትመት ያበቁት የቀድሞው ጦር ሠራዊት አባል አቶ ገስጥ ተጫኔ እንደሚሉት አገር ታፍራና ተከብራ የምትቀጥለው የተደራጀ ጠንካራ ወታደርና ብሔራዊ ስሜት ያለው ማኅበረሰብ ሲፈጠር ነው።
ከደርግ መንግስት በፊት የውትድርና ሙያ የሚወደድ፣ በሕዝቡም ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የሚቸረው እንደነበር ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አውስተዋል።
ኢትዮጵያ የምስራቁን ርዕዮተ ዓለም አቋም ስትይዝ ወታደርና ፖሊስን የመንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ አድርጎ የሚወስድ ትርክት በመፈጠሩ ወደ ውትድርና የመግባት ፍላጎት እየቀነሰ ስለመምጣቱ ይናገራሉ።
በርካታ ታሪካዊ ጠላቶች ያሏት ኢትዮጵያ የጦር ሠራዊቷን ማጠናከር እንዳለባትና በዚህም ብሔራዊ ስሜትና የአገር ፍቅር ማምጣት ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል ታሪክ ተመራማሪው።
ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ፣ የትምህርት ተቋማትና መንግስት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
ከሰው ሀይል በተጨማሪ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ሠላም ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት በትጥቅ ራሱን የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ነው ያመለከቱት።
ኢትዮጵያ በወታደራዊ ትጥቅ ጥገኝነት ሳቢያ ተደጋጋሚ ችግር ገጥሟት እንደነበረ በማንሳት በአድዋ፣ በ1956 እና 1969 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ወቅት ያጋጠመውን የጥይት እጥረት በአስረጂነት ያነሳሉ።
በመሆኑም ጦር ሠራዊቱ ከውጭ ቴክኖሎጂ ጥገኝነት ወጥቶ ትጥቁን ራሱ አሟልቶ በሚደራጅበት ወታደራዊ ግንባታ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በደርግ ዘመን ጦር ሠራዊቱ በቴክኖሎጂ ራሱን እንዲችል ጅምር መሰረተ ልማቶች እንደነበሩ በማስታወስ እነዚህ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በግላቸው በህወሓት የ27 ዓመታት ቆይታ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠንካራ ነው የሚል እምነት እንዳልነበራቸው የሚገልጹት አቶ ገስጥ ከለውጡ በኋላ ግን የመከላከያ መዋቅርና አደረጃጀት ተፈጥሯል ይላሉ።
ይህም በህወሓት ቡድን ላይ በተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ሠራዊቱ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ንጹሃን ሳይጎዱ ድል ማድረጉ በተግባር የታየ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሕግ ማስከበር ተልዕኮው የተመራበት መንገድም የሚያረካ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህ ወታደራዊ አቅም ግንባታ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።