ኤጀንሲው ባለፉት 10 ዓመታት 250 ጥናቶችና 48 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ስራ ላይ አውሏል - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው ባለፉት 10 ዓመታት 250 ጥናቶችና 48 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ስራ ላይ አውሏል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ባለፉት አስር ዓመታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ 250 ጥናቶችና 48 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ።
በእርሻ ላይ የተገደበውን ተግባሩን ወደ እንስሳት ዘርፍ በማሳደግም ይሰራል ተብሏል።
ኤጀንሲው ያለፉትን አስር ዓመታት አፈጻጸሙንና በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ያዘጋጀውን ስትራቴጅክ እቅድ ይፋ አድርጓል።
የግብርና ግብዓት በማቅረብ፣ የግብርና ኤክስቴንሽን በማስፋፋትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ውጤታማ ስራዎች በኤጀንሲው መከናወኑን የኤጀንሲው ዳይሬክተር ካሊድ ቦምባ ገልጸዋል።
በተጠቀሰው ዓመት ግብርናውን የማዘመን ሂደቱን ተደራሽ በማድረግ በርካታ አርሶ አደሮች ከራሳቸው አልፈው ምርታቸውን ለገበያና ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ማቅረብ መቻላቸውንም ተናግረዋል።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በክላስተር ማረስ፣ ምርጥ ዘር መጠቀም የምርት ብክነትን መቀነስ፣ በመስኖ እና በጉድጓድ ውሃ በመጠቀም አርሶ አደሩ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡንም አክለዋል።
ከዚህ በፊት በእርሻ ላይ ብቻ የተንጠለጠለውን ስራ ወደ እንስሳት ዘርፍ በማሳደግ ምርቶቹን በዘመናዊ መንገድ የማቀነባበር ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በኤጀንሲው የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ በበኩላቸው በቀጣይ አስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ግብርናውን ሜካናይዝድ በማድረግ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ተግባራዊ እንደሚደረግ አንስተዋል።
በዚህም አነስተኛ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እርሻ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን በመጠቀም እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።
ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በ10 የሰብል ዝርያዎች ላይ በማተኮር በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
አራቱ ክልሎች ከአገሪቱ የግብርና ስራ 80 በመቶው የሚካሄድባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ኤጀንሲው በቀጣይ ወደ ሁሉም ክልሎች የማስፋት ስራ በማከናወንና በከተማ ግብርና ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
በቀጣዮቹ አስር ዓመታት 6 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የዘመናዊ እርሻ ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ዶክተር ይፍሩ ተናግረዋል።
የግብርና ዘርፍ ሁሉን አካታችና ቀጣይነት ያለው እንዲሆንና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን ተናግረዋል።
በዚህም የግብርና ዘርፉ ለተከታታይ ዓመታት ዕድገት በማሳየት ለአገሪቱ ጥቅል ምርት እድገት ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖረው የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል ።
ኤጀንሲው በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የተሻለ ስራ በመስራት ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን አስተዋዕጾ ለማበርከት መዘጋጀት ይጠበቅበታል ብለዋል።