ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኪነ ጥበብን ለአገር አንድነትና ለልማት ለማዋል እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2013 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኪነ ጥበብን ለአገር አንድነትና ለልማት ለማዋል እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

በቢሮው የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪ የማበልፀግና የማስፋፋት ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ቦጋለ እንዳስረዱት ቢሮው ኪነ ጥበብን ለአገር ዕድገትና ለሕዝቦች አንድነት ለማዋል አትኩሮ በመስራት ላይ ነው።

በዚህም ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመመስረት የጥበብ ሥራዎችን ለማውጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በመዲናዋ የተዳከመው የኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኪነ ጥበብ ተቋማት እንዲስፋፉና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ለጀማሪ ክበባትና የባህል ቡድኖች በዕውቀት ላይ የተደገፉ ሥራዎች እንዲያቀርቡ  በመደገፍ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

“በአዲስ አበባ ከተማ ኪነ ጥበቡ በተፈለገው ልክ እያደገ አይደለም” ያሉት አቶ አስቻለው፣ የኪነጥበብ ማዕከላት በከተማዋ የተለያዩ ሥፍራዎች ለመክፈት መታቀዱን ጠቁመዋል።

በዚህም በብዛት በመሃል ከተማ ላይ ያተኮረውን የጥበብ ማዕከላት ስርጭት ለማስተካከል ያስችላል ብለዋል።

የዘርፉን የሰው ኃይል ለማጠናከር እንደሚረዳም ተናግረዋል።

ቢሮው  ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰልጣኞችን በሙዚቃ መሣሪያ፣ በድምፅ፣ በውዝዋዜ፣ በቴአትር፣ በሥነ-ጽሑፍና በፊልም ዘርፎች እያሰለጠነ ይገኛል።

ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ከሚሰጠው ሥልጠና በፊልም ዘርፍ 30 ሰዎች ስልጠናውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም