ቀጥታ፡

በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ለማስቀረት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2013 (ኢዜአ) በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ለማስቀረት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ።

ዓለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ ላለፉት 15 ቀናት በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል።

በዓሉ በአለም ለ29 ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ብርቱካን አህመድ እንደገለጹት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ለማስቀረት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

ለዚህ ይረዳ ዘንድ ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን የኢኮናሜ ጫና በመቀነስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለይ የሴቶች ድርሻ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።

የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ስራ ወንጀለኞችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

ፆታዊ ጥቃት አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጫና በማድረስ ተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮናሚያዊ ችግር ስለሚዳርጋቸው ችግሩን ለመቅረፍ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል ።

ፕሮግራሙን የታደሙት መምህር ዳመነ ሞገስ በበኩላቸው በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለማስቀረት መንግስትን ጨምሮ ሁሉም አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው ብለዋል ።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶችና ህጻናት ምርመራ ክፍል ሃላፊ ኢንስፔክተር ሲሳይ መንግስቱ "አሁን ላይ ወደ ጣቢያ በመምጣት የደረሰባቸውን ጥቃት የሚያመልክቱ ሰዎችን መሰረት በማድረግ በሴቶች ላይ የሚደረሰው ጥቃት ቀንሷልም ጨምሯልም ማለት እንደማይቻል" ገልጸዋል።

ህጻናትና ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ በንቃት መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበው የሚመለከታቸው አካላት ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት ጥቃቱን በመከላከልና በመቆጣጣር ላይ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በአሉ ከህዳር 15 እስከ 30 በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ሲከበር ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም