ቀጥታ፡

መቀሌ ከተማ ተቋርጦባት የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በነገው እለት ስራ ይጀምራል

አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2013 (ኢዜአ) በጥፋት ሃይሉ ተቋርጦ የነበረው የመቀሌ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠግኖ ከነገ ጀምሮ አገልግሎቱን እንደሚጀምር የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለፁ።

መንግሥት ጁንታው ያወደማቸውን የመሰረተ ልማት ተቋማት መልሶ ለመገንባት ርብርብ ያደርጋልም ብለዋል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ በሰጡት መግለጫ ጁንታው በክልሉ በርካታ በሰረተ ልማቶችን በማውደም ህዝቡን ለችግር ዳርጓል።

ጁንታው በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ባደረሰው ጉዳት የመብራት አገልግሎት መቋረጡን ገልጸው ለጥገና በተደረገው ርብርብ ከነገ ጀምሮ መቀሌ አገልገሎት ታገኛለች ብለዋል።

ቡድኑ የመሰረተ ልማቶቹ በአጭር ጊዜ እንዳይጠገኑ አድርጎ ማውደሙንም ተናግረዋል፡፡

ሆኖም መንግሥት ባለው አቅም የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን በተለይ የስልክና መብራት በሰረተ ልማቶችን በርብርብ በመጠገን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የኤሌክትሪክ፣ የውሃ ፣የቴሌኮም አገልግሎት ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በኤሌክትሪክ ማስተላላፊያ መሥመሮች ላይ እየተደረገ የሚገኘው ጥገና በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ መቀሌ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ታገኛለች ብለዋል።

ሌሎች የክልሉ ከተሞችም በአጭር ቀናት ውስጥ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ዶክተር አብርሃም ገልጸዋል፡፡የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ትግራይ ክልል የተዘረጉት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መሥመሮችን እየጠገነ መሆኑን ሰሞኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም