ኢትዮጵያ ትላልቅ የስፖርት ኩነቶችን ማስተናግድ እንደምትችል አይተናል... የአኖካ ዋና ጸሐፊ አቡ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ትላልቅ የስፖርት ኩነቶችን ማስተናግድ እንደምትችል አይተናል... የአኖካ ዋና ጸሐፊ አቡ አህመድ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ትላልቅ የስፖርት ኩነቶችን ማስተናግድ እንደምትችል ያየንበት አጋጣሚ ነው ሲሉ የአኖካ ዋና ጸሐፊ አቡ አህመድ ገለጹ።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደው የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ጉባኤ /አኖካ / ስኬታማ እንደነበርም በተሰጠው መግለጫ ተጠቅሷል።
የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ጉባኤ ህዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ መደረጉ ይታወቃል።
በጉባኤው ላይ ከ250 በላይ የተለያዩ አገራት ተወካዮች መሳተፋቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
የአኖካ ዋና ጸሀፊ አቡ አህመድ ጉባኤው በተሳካ መልኩ መካሄዱን ገልጸው፤ በቀጣይም ኢትዮጵያ ትላልቅ የስፖርት ኩነቶችን ማስተናግድ እንደምትችል ያየንበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጉባኤውን ለማስተናገድ ያደረገውን ጥረት አድንቀው ተሳታፊዎች በጥሩ ሁኔታ መስተናገዳቸውንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው "ጉባኤው ስኬታማና ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ያግዛል" ብለዋል።
በዚህም ኮቪድ-19ን በመጠንቀቅ ስብሰባዎችን ማዘጋጀት እንደሚቻል በማሳያት ሌሎች ሀገሮች ከዚህ ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በተደረገላቸው መስተንግዶ የተደሰቱ የጉባኤው አባላት ቀጣዩን ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታስናግድም ፍላጎታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።
ለዚህ ጉባኤ መሳካት አስተዋጽኦ የነበራቸው የኢፌዴሪ መንግስትና ሌሎችም ባለድርሻ አካለትን አመስግነዋል።