ህዝቡ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ እያደረገው ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

137
አዲስ አበባ ሀምሌ 12/2010 ህዝቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረገው ያለው ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ገለጸ። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር እያደረገችው ያለው የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት ደግሞ ለግድቡ ግንባታና ለሁለቱ አገራት እድገት የበለጠ ጉልበትና መተማመን አንደሚፈጥርም ተገልጿል። የግድቡ ግንባታ ሂደት በአሁኑ  ወቅት ቀንና ሌሊት እየተፋጠነ ሲሆን ግንባታውም 66 በመቶ መድረሱም ተገልጿል። የጽህፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደተናገሩት የህዳሴ ግድቡ "የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለአንድ ዓላማ በህብረት እንዲሰለፉ  ምክንያት" መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ላይ ደግሞ የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል። ለአብነትም በ2010ዓ.ም ከህብረተሰቡ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለመሰብሰብ ታቅዶ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ በመምጣቱ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ነው አቶ ኃይሉ የገለጹት። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ አገራዊ አንድነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ የህዝቡም ድጋፍ የበለጠ እንዲነቃቃ አድርጎታል ብለዋል። በተለይም አገሪቷ ከኤርትራ ጋር እያደረገችው ያለው የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት ለግድቡ ግንባታና ለሁለቱ አገራት እድገት የበለጠ ጉልበትና መተማመንን እንደሚሰጥም ተናግረዋል አቶ ኃይሉ። የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ከህዝቡ መሰብሰቡን ጽህፈት ቤቱ ያስታወቀ ሲሆን፤ ህዝቡ በቀጣይም ለህዳሴ ግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጽህፈት ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም