የህወሃት ቡደን የሴራ ፖለቲካ መክሸፍ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይቻል ያረጋገጠ ነው --- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃት ቡደን የሴራ ፖለቲካ መክሸፍ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይቻል ያረጋገጠ ነው --- ምሁራን
ደሴ ታህሳስ 1/2013 (ኢዜአ) የህውሃት ቡድን የሴራ ፖለቲካ የከሸፈበት መንገድ በህዝቦቿ አጥንትና ደም የተገነባች ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይቻል ያረጋገጠ የድል ምዕራፍ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋሻው መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዜጎቿ አንድነት የተገነባች ታላቅ ሃገር ናት።
"ይሁን እንጂ በዲሞክራሲ ስም ህዝብን በማታለል ኢትዮጵያዊያን በከፈሉት ዋጋ ወደ ስልጣን የመጣው የህወሓት ቡድን በሚያራምደው የሴራ ፖለቲካ ህዝብን በዘርና በሐይማኖት ሲከፋፍልና ሀገር ለማፍረስ ሲጥር ኖሯል" ብለዋል።
"ቡድኑ በዘራው የተንኮል ሴራ ዜጎችን ለአፈና፣ ለግድያ፣ ለስደትና ለመፈናቀል ሲዳረጉና ህዝቡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፅምበት ቆይቷል" ሲሉም ተናግረዋል።
ሀገር ፀንታ እንዳትቀጥል ከፋፋይ ሃሰቦችን በመዝራት ሰይጣናዊ ስራዎች መፈጸሙንም ጠቅሰዋል።
ቡድኑ የክፋት ሴራው አይሎ የሀገር ሉአላዊነት መገለጫ በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እስከመፈጸም በመድረሱ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከማስቆጣቱ በላይ በመንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ የተወሰደበት መሆኑን ጠቅሰዋል ።
"ቡድኑ በተወሰደበት የህግ ማስከበር እርምጃ የሴራው ፖለቲካ ከሽፎ መወገዱ ለዘመናት የተገነባው ኢትዮጵያዊነት አሸንፎ ወደ ማይመለስበት መቃብር ሊወርድ ችሏል" ብለዋል።
ቡድኑ የተሸነፈበት መንገድ ኢትዮጵያን በማንኛውም መንገድ ማፍረስና አንድነቷን መናድ እንደማይቻል ያረጋገጠ የድል ምዕራፍ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከተገኘው ድል በመማር ኢትዮጵያን ታሪኳን ሊመጥን የሚችል የፖለቲካ ምህዳር መዘርጋት እንደሚገባ ምሁሩ አመላክተዋል።
"የህወሓት ቡድን በዲሞክራሲ ስም ህዝቡን ሲከፋፍልና ሀገር ለማፍረስ ሲሰራ የኖረ ድርጅት ነው" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ባልቻ ናቸው።
"ቡድኑ ሀገር በእውቀት እንድትመራ የሚያደርገውን ምሁር በፖለቲካ ሴራ በማሳደድና በመግደል ሀገሪቱን ምሁር አለባ ለማድረግ አልሞ ሲሰራ ቆይቷል" ብለዋል።
''ቡድኑ የተንኮልና የግፍ መጨረሻው እንዲህ አይነት ውድቀት ነው'' ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ የቡድኑ መውደቅ በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር የሚፈጥር መሆኑን አመላክተዋል።
"አሁን ላይ ልጓም ያለውና ኢትዮጵያን ዳግም በመሰል ችግር ውስጥ እንዳትወድቅ የሚያደርግ የፖለቲካ አካሄድ መዘርጋት ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።
"በተለይ ልቅ የሆነው የፌደራልና የክልል መንግስት ግንኙነትም መስተካከል ይገባዋል"ብለዋል ።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ ኢትዮጵያ ከችግሮቿ ተላቃ ህዝብ ያለ ስጋት በአንድነት የሚኖርባት፣ በየትኛውም አካባቢ ሰርቶ ሀብት ማፍራት የሚቻልባት ሀገር እንድትሆንም ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ የሃሳብ ገበያውን ማመቻቸት ይገባል።
ወጣቱ ሃይል የሀገሩን ጥንታዊ ታሪክ በሚገባ በመረዳት በሰከነና በተረጋጋ መንገድ ለሀገር ግንባታው የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
የህወሓት ቡድን በፈጸመው የሀገር ክህድት ወንጀል መንግስት የወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ እንደ ቀድሞ አባቶች ታሪክ ለሌሎች የሃገር ውስጥና የውጭ ጠላቶች አስተማሪ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰሩ አስታውቀዋል።