ቀጥታ፡

በህወሃት ጁንታ ጉዳት የደረሰበት የአላማጣ መቀሌ 141 ኪሎ ሜትር የኤሌትሪክ መስመር ጥገና በመገባደድ ላይ ነው

ታህሳስ 1/2013 (ኢዜአ) በህወሃት ጁንታ ጉዳት የደረሰበት የአላማጣ መቀሌ 141 ኪሎ ሜትር የኤሌትሪክ መስመር ጥገና ስራ 70 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የሰሜን ሪጅን አስታወቀ።

በአገር መከላከያ ሰራዊት የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ መቋቋም የተሳነው ቡድን የትግራይን ህዝብ መሰረተ ልማት በማውደም ጉዳት ማድረሱም ይታወቃለ።

የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የተለያዩ መንገዶች፣ ድልድዮችና የኤሌክትሪክ ገመዶችን የጁንታው ታጣቂ ሃይል አውድሟል።

የኢትጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የሰሜን ሪጅን ትራንስሚሽን ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ አየልኝ እንዳሉት፤ የኤሌክትሪክ መስመሩ ከ25 በመቶ በላይ ወድሞ ነበር።

“ጥገና የሚካሔድበት የአላማጣ መቀሌ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪ ቢሆንም ችግሩን ተቋቁመን ሌት ከቀን በመስራታችን የጥገና ስራው አሁን ላይ 70 በመቶ ደርሷል” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ማይጨውን ጨምሮ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ከተሞች የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።የአላማጣ መቀሌ የኤሌትሪክ መስመር ጥገናን እስከ መጭው ቅዳሜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም