ቀጥታ፡

የሕወሐት ጁንታ የኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ጣቢያዎች ላይ ጉዳት በማድረስ ማቋረጡ ተገለጸ

ታህሳስ 1 / 2013 (ኢዜአ) የሕወሐት ጁንታ የኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ጣቢያዎች አገልግሎት በማቋረጥ ጉዳት ማድረሶን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።

በ14 ቀናት ውስጥ ብቻ በተለያዩ ተቋማት ላይ 39 ነጥብ 8 ቢሊዮን ጊዜ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መፈፀሙም ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በሰሜን ሪጅን የቴሌኮም አገልግሎት ላይ የደረሰውን መስተጓጎል አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሰሜን ሪጅን የአገልግሎት መቋረጡ የተከሰተው በመቀሌና በሽሬ የሚገኙ ዋና ጣቢያዎችን አማራጭ የመገናኛ መስመሮች  በሙሉ በመቁረጥና የኮመርሻል ኃይል አቅርቦት በማቋረጥ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ ያቋረጠው የህወሐት ጁንታ መሆኑን ከኮር ሳይት በተገኙ የደህንነት ካሜራዎችና ሲስተሞች ማረጋገጥ መቻሉን ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

ከተገኘው መረጃ በመነሳት" ከተቋሙ የጥበቃ አባሎች ውጭ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ልብስ የለበሱ አካላት ወደ ጣቢያዎቹ በመግባት አገልግሎቱን የማቋረጥ ድርጊት እንደፈፀሙ ማረጋገጥ ተችሏል" ነው ያሉት።

በዕለቱ በሰሜን ሪጅን ላይ የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጡን የሚጠቁም መረጃ በማዕከል ከሚገኘው የኔትወርክ መቆጣጠሪያ ሲስተም ለቴክኒክ ቡድንና ለከፍተኛ አመራሩ እንደደረሰ ስራ አስፈፃሚዋ አብራርተዋል።

አገልግሎቱ መቋረጡን የሚጠቁመው መረጃ ከደረሳቸው በኋላ የተከሰተውን ሁኔታ በማጤን በአገራዊ ኔትወርክ ላይ አደጋ እንዳያስከትል የጥንቃቄ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በሪጅኑ ያለውን ሁኔታ ለመፈተሽና አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም አገልግሎት ለማስጀመር ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ገልፀዋል።

አገልግሎቱ ከመቋረጡ በተጨማሪ በ14 ቀናት ውስጥ በመንግስት ተቋማት፣ በትምህርት፣ በፋይናንስ፣ በመገናኛ ብዙሃን እና በቴሌኮም መሰረት ልማት ላይ ያነጣጠረና 39 ነጥብ 8 ቢሊዮን ጊዜ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መፈጸሙንም ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

ሆኖም ጥቃቶችን በማምከን በአገር ደህንነትና ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የነበረውን አደጋ መከላከል መቻሉን ስራ አስፍፃሚዋ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የቴሌኮም አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የተጎዱ መስመሮችን በመጠገን በዳንሻ፣ በተርካን፣ በሁመራ በሽራሮ፣ በማይፀብሪ፣ በማይካድራ እና በኮረም በከፊል አገልግሎት መስጠት የተጀመረ ሲሆን በአላማጣ ሙሉ በሙሉ የቴሌኮም አገልግሎት መጀመሩን ተናግረዋል።

የኃይል መቋረጥ፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች መቆራረጥ፣ እና የሰው ኃይል ለማሰማራት ምቹ ሁኔታ አለመኖር አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር ተግዳሮት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።

ችገሮችን ለመፍታትና የቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ለማስጀመር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከፀጥታ አካላት እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ስራ አስፈጻሚዋ በመግለጫቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም