ቀጥታ፡

በሴቶችና ህጻናት ላይ የመፈጸም ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ጎባ ታህሳስ 1 / 2013 (ኢዜአ) በሴቶችና ህጻናት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

 "በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የማይታገስ ትውልድ እንፍጠር"መሪ ሀሳብ የነጭ ሪቫን ቀን  በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ  ዛሬ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር በዛብህ ወንድሙ  በወቅቱ እንደገለጹት ተቋሙ  ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ በሚያካሄደው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ መረሃ ግብሮች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፉን በበላይነት የሚከታተል ዳይሬክቶሬት በተቋሙ ከመክፈት በተጓዳኝ በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ጉዳዮች ላይ በግንባር ቀደምትነት እንዲሰተፉ እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡ 

በሴቶችና ህጻናት  ላይ እየደረሰ ያሉ ፆታዊ ጥቃቶችና ትንኮሳ በተወሰኑ አካላት ብቻ መከላከል  ስለማይቻል በተለይም የሃይማኖት መሪዎች፣ መምህራንና ሌላውን ህብረተሰብ ቅንጅት በመስራት  የበኩላቸውን እንዲወጡ  ዶክተር በዛብህ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሴቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሊዲያ ተካ በበኩላቸው በሴቶችና ህጻናት ላይ የአስገድዶ መድፈር፣ ትንኮሳ፣ ጠለፋና ሌሎች ጥቃቶች እየደረሱ ነው ብለዋል።

ሴቶችና ህጻናት ደህንነታቸው ተጠብቆ በሃገራቸው ልማት ላይ ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ከማንኛውም ጥቃት ሊጠበቁ  እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመው ዳይሬክቶሬትም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስና ተሳትፏቸውንም ለማሰደግ ከተቋሙ  ማህበረሰብና ሌሎች  ባለድርሻ አካት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ ወጣት  ኤልዲያና ሱሌይማን በሰጠችው አስተያየት የነጭ ሪቫን ቀን በሚከበርባቸው ቀናት የሚመለከታቸው አካላት ፆታዊ ጥቃቶችን በመከላከል አጋርነታቸውን በተግባር ማረጋገጥ ይገባቸዋል ብላለች፡፡

ሴቶችም በተሰማሩበት ሁሉም የሙያ መስክ ውጤታማ በመሆን ብቃታቸውን በማስመስከር ሊደርስባቸው ከምችሉ ትንኮሳዎች ራሳቸውን ሊከላከሉ እንደሚገባም አመልክታለች፡፡ 

ጥቃት የሚፈጽሙ አካላትን በህግ ፊት እንዲጠየቁና ጠበቅ ያለ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ቢደረግ ትንኮሳው ይቀንሳል የሚል እምነት አለኝ ያሉት  ደግሞ ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ሀረግዌይን በረደድ ናቸው፡፡ 

በፓናል ውይይቱ  የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች፣ መምህራን፣ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው የባሌ ዞን ሴክትር መስሪያ ቤት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ 

የነጭ ሪቫን ቀን  በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት ለመከላከል ወንዶች አጋርነታቸውን  በተግባር እንዲያሳዩ ለማነሳሳት የሚከበር እንደሆነ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም